መታመን እስከ መስዋእትነት

         libse haile mariam

ሰሜን ወሎ ዞን መቄት ወረዳ ገረገራ 02 ቀበሌ ነው ተወልዳ ያደገችው፤ ዕውቀት እንድትቀስምና በጠንካራ ስብዕና እንድትገነባ ካሕን አባቷ ከዕድሜ እኩዮቿ ጋር ትምሕርት ቤት ላኳት፡፡ አካል ጉዳተኛነቷ፣ ሴትነቷ እና የአካባቢው መልከዓምድር ከመማር አላገዳትም፤ ችግሮቿን ተቋቁማ ትምሕርቷን አጠናቀቀች፤ አባቷ የሠነቁትን ልጆቻቸውን አስተምሮ ለወግ ማዕረግ የማድረስ ህልም አሳካች፤ የዛሬ ባለ ታሪካችን ወይዘሪት ልብሴ ኃይለማርያም፡፡

ልብሴ በጸሐፊነት እስከ ደረጃ አራት ተምራለች፤ በሥራ ላይ እያለችም የመጀመያ ዲግሪዋንም በማኔጅመንት ተምራ አጠናቃለች። በተማረችው ትምሕርት የአካባቢዋን ማኅበረሰብ ለማገልገል በነበራት ጽኑ ፍላጎት 2010 . አመልድ ኢትዮጵያ መቄት ወረዳ ቅርንጫፍ ሥራ ሲጀምር በጸሐፊነት እና በንብረት ክፍል ባለሙያነት ተቀጠረች።

ወይዘሪት ልብሴ አመልድ ኢትዮጵያን በማገልገል አምስት ዓመታት አስቆጥራለች። በእነዚህ ዘመናት ድርጅቱ በዝናብ አጠር ወረዳዎች የሚኖሩ፣ ሰው ሠራሽ እና የተፈጥሮ አደጋ ያጋጠማቸውን የማኅበረሰብ ክፍሎች ያለ አድልኦ ሲያግዝና ሲያቋቁም ተመልክታለች። ለብዙዎች የክፉ ቀን ደራሹ ድርጅት ነሐሴ 2013 . ሽብርተኛው የትግራይ ወራሪ ቡድን አማራ ክልልን ሲወር የጥፋት ዒላማ ኾነ።

የሽብርተኛው የትግራይ ወራሪ ቡድን አባላት በለመደ እጃቸው የድርጅቱን ሃብት እና ንብረት ለመዝርፍ እጃቸውን መዘርጋታቸው አልቀረም። ወይዘሪት ልብሴ ለአምስት ዓመታት እንጀራ የበላችበት፣ የአካባቢዋን ማኅበረሰብ ከተለያዩ ችግሮች የታደገውን ድርጅት ሲዘረፍ ቆማ መመልከት አልፈቀደችም። ወይዘሪት ልብሴ የድርጅቱ መዘረፍ ከእሷ አልፎ ሌሎችን እንደሚጎዳ ስትረዳ አምስት ኮምፒውተሮች፣ 12 የቅየሳ መሳሪያዎች (ጂፒኤስ) እና አንድ ፕሪንተር በመደበቅ ከዝርፊያ እና ውድመት አድናለች፤ ከዘበኞች ጋር በመመካከርም የድርጅቱን ታፔላ በመንቀል የድርጅቱ ቢሮ መኖሪያ ቤት በማስመሰል ድርጅቱ የከፋ ጉዳት እንዳይደርስበት ኀላፊነቷን ተወጣች።

አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች ባሳረፉበት ብርቱ ክንድ ተቀጥቅጦ ከአካባቢው ተጠራርጎ ወጣ፤ የሚደመሰሰውም ተደመሰሰ፡፡ ወይዘሪት ልብሴ እና ሲያግዟት የነበሩ ኹለቱ ጥበቃዎችም ቀን ወጣላቸው። በአደራ የሠጣቸው ሰው ባይኖርም ክፉ ቀን እስኪያልፍ ብለው ቤት ያስቀመጡት ንብረት ለባለቤቱ የሚያስረክቡበት ጊዜ ደረሰ፤ ደስም አላቸው።

ከወረራው በኋላ የጉዳቱን መጠን የሚያጠና ቡድን ወደ ቦታው ተላከ። ቡድኑም ወይዘሪት ልብሴ ኀይለማርያም ከዘረፋ ያዳነችው ንብረት በአጥኝው ቡድን ሲተመን 87 ሺህ ብር በላይ ኾነ።

የሽብር ቡድኑ አባላት የደበቀችውን ንብረት ቢያገኙባት የሚደርስባትን ስቃይ ታውቀዋለች፤ የሕይዎት መስዋእትነት ጭምር ሊያስከፍላት ይችል ነበር፤ ነገር ግን በታማኝነቷ ፀንታ ተገኝታለች፤ ሕይዎቷን ቀብድ አስይዛ የሕዝብ ንብረት ከጨካኞች ታድጋለች፤ መታመን ይሏል ይህ ነው።

ምንጭ፡- አሚኮ

Copyright © 2012 ORDA Ethiopia.
All Rights Reserved.