አመልድ ኢትዮጵያ በጦርነት ቀጠናዎች ባሉ ፕሮጀክቶች ሆነው በታማኝነት ህዝብን ላገለገሉና ንብረትን ከውደመት ለታደጉ ሰራተኞች እና ተባባሪ አካላት የእውቅና ሽልማት ሰጠ

     winner

2013 . ለመላው ኢትዮጵያዊያን በተለይም የሰሜኑ ክፍል በጦርነት የደቀቀበት እና በታጣቂ ሐይሎች የህዝቦች መፈናቀል፣ መገደል፣ መደፈር፣ መዘረፍ እና ከፍተኛ የሆነ የመሰረተ ልማት ውድምት የደረሰበት ዓመት ነበር፡፡ በተለይም በኢትዮጵያ መንግስት አሸባሪ ተብሎ የተፈረጀው ትህነግ (TPLF) በአማራ ክልል እና አፋር ክልል በታቀደ እና በተጠና መልኩ ትምህርት ቤቶችን፣ ጤና ጣቢያዎች እና የህዝብ መገልገያ ተቋማትን በመዝረፍ የቀረውን አውድሟል፡፡ በዚህም አመልድ ኢትዮጵያ የተሰማራባቸው አካባቢዎች ያሉ ህዝቦች የከፋ ችግርን ቀምሰዋል፡፡

የጦርነቱ ቦታዎች የአመልድ ኢትዮጵያ ፕሮጀክት /ቤቶች በብዛት የሚገኙባቸው በመሆናቸው ድርጅቱ 87 ሚሊየን ብር በላይ ሃብት ውድመት ደርሶበታል፡፡ እንግዲህ በዚህ ሁሉ የጦርነት ምስቅልቅል ውስጥ ሆነው በተሰጣቸው ኃላፊነት 27 ሚሊዮን ብር በላይ የድርጅታቸውን ንብረት ከዘረፋ እና ከውድመት የታደጉ ምስጉን፣ ታማኝ እና ቅን 38 ሰራተኞች እና ተባባሪ አካላትን ለማበረታታት የእውቅና ሽልማት በባሕር ዳር ከተማ ተሰጥቷል፡፡

     DSC 1901

የአመልድ ኢትዮጵያ ዋና ሥራ አስኪያጅ አለማየሁ ዋሴ (/) የእውቅና ሽልማቱን በተመለከተ የሚከተለውን መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

“አመልድ ኢትዮጵያ በአማራ ክልል ገጠርና ደሀ ተኮር የሆነ ኘሮጀክቶችን በመንደፍ በርካታ ዜጐች ከድህነት ለማላቀቅ የሚያደርጉትን ጥረት በመደገፍ ተጨባጭ ለውጥ ሲያመጣ ቆይቷል፡፡ የአካባቢ ጥበቃ ሥራዎችን በማከናወን የግብርና ልማት እንዲጨምር፣ የውሃ አጠቃቀማችን እንዲሻሻል በርካታ ተግባራቶችን አከናውኗል፡፡ በኘሮግራሞቹ ሴቶች፣ የአካል ጉዳተኞችና ወጣቶች የልማቱ እኩል ተጠቃሚ እንዲሆኑ ልዩ ትኩረት ሠጥቶ ሲሰራ ቆይቷል፡፡ ሰው ሰራሽ የተፈጥሮ አደጋዎች በተከሰቱ ጊዜም በርሓብ የሰው ሕይወት እንዳይቀጠፍ የቤተሰብ ጥሪት እንዳይሟጠጥ የዕለት ዕርዳታ በማቅረብ መልሶ በማቋቋም ከፍተኛ ጫና እየተጫወተ ይገኛል፡፡

ይሁን እንጅ የህወሀት ታጣቂ ቡድን በአማራ ክልል ባደረገው ወረራ የድርጅቱ የልማትና የዕለት ዕርዳታ ሥራዎች ወረራ በተፈፀመባቸው አካባቢዎች ነጻ እስኪወጡ ድረስ ተቋርጦ የነበረ ሲሆን ከወረራው መቀልበስ በኋላ በተደረገው የሰውና የንብረት ቆጠራ በድርጅታችን ሠራተኞችና ንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱን ተገንዝበናል፡፡ የድርጅቱ ታታሪ ሠራተኞች የነበሩ 3 ባለሙያዎች (1 ሴት እና 2 ወንዶች) በታጣቂዎች በግፍ የተገደሉ ሲሆን ሁለቱ እስከአሁን ድረስ የደረሱበት አልታወቀም፡፡ ይህ ድርጊት በሰብዓዊ አገልግሎት ላይ የተሰማራን ሰው መግደል በምንም መመዘኛ ተቀባይነት የሌለው ሲሆን ድርጅታችን በእጅጉ ያሳዘነና የጎዳ ክስተት ሆኖ አልፏል፡፡

በተጨማሪም የአመልድ ኘሮጀክት /ቤቶችና የእርዳታ እህል መጋዘኖች የጥቃቱ ሰለባ በመሆናቸው 80 ሚሊዮን ብር የሚገመት የቢሮና የመጋዘን የመስክ መገልገያ ንብረቶችና እህልና ምግብ ዘይት በታጣቂው ቡድን የተዘረፉ ሲሆን የኘሮጀክት /ቤቶችና መጋዘኖችም ውድመት ደርሶባቸዋል፡፡

በዚህ ሁሉ የግድያና የዘረፋ ጥቃት በርካታ የድርጅቱ ሠራተኞች ለሕይወታቸው ሳይሳሱ 11 ሚሊዮን ብር የሚገመት ንብረት በመደበቅና በማሸሽ ከዘረፋና ከውድመት ታድገዋል፡፡ በዛሬው ዕለት የምንሸልማቸው እነዚህ ሠራተኞቻችን ከፍተኛ የሞራል ብቃት ያሳዩ፣ የታማኝነትን ጥግ ያመለከቱ፣ ለሀገርና ለወገን ተቆርቋሪነታቸውን ያስመሰከሩ፣ በመሆናቸው አመልድ ኢትዮጵያ እንደነዚህ ያሉ ሠራተኞች ያሉት በመሆኑ ኩራት ይሰማናል፡፡

ውድ የዛሬው ተሸላሚ የሥራ ባልደርቦቻችን! እንደ እናንተ ያሉ ታማኞችና ሥራ ወዳድ የስራ ባልደርባ ማግኘት እድለኝነት ሲሆን ላደረጋችሁት ሁሉ ከቃላት በላይ የሆነ ምስጋናዬ በድርጅቱ ስም አቀርብላችኋለው፡፡ ይህንን የሽልማት መርሀ ግብር ለማዘጋጀት ከሚጠየቀው የገንዘብ ወጭን ሳይጨምር ድርጅታችን አመልድ ለእነዚህ 38 ሠራተኞቹ በገንዘብ ሽልማት ለመስጠት ከግማሽ ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ አውጥቷል፡፡

ይሁን እንጅ በዛሬው ዕለት የምንሰጣቸው የገንዘብና የምስክር ወረቀት ሽልማት በጎነታቸውን ለመዘከር ብቻ እንጅ የሞራል ከፍታቸውንና ታማኝነታቸው የሚመጥን ይሆናል ብለን አናምንም፡፡ ስለሆነም በድርጅቱ ውስጥ በሚኖሩ ዕድገቶችና ዕድሎች ሁሉ ለወደፊቱ ቅድሚያ የሚሰጣቸው መሆኑን ማረጋገጥ እወዳለሁ፡፡

ከሠራተኞቻችን በተጨማሪ ልዩ ልዩ ተቋማትና ግለሰቦች አመልድ ኢትዮጵያ የሕዝብ ተቋም ነው፤ ድሆችን ለማገዝ የሚተጋ ድርጅት ስለሆነ ንብረቱ ሊዘረፍ አይገባም በማለት አስቸጋሪዎቹን ወራት የድርጅቱን ንብረት እንዳይዘረፍ የተከላከሉና ከለላ የሰጡ መሆናቸውን ስንገልፅ ትልቅ ክብር ይሰማናል፡፡

ከእነዚህ ተቋማት መካከል ብልጫ ያሳዩትን ብቻ በዛሬው ዕለት እውቅና ለመስጠት የጋበዝን ሲሆን ለእነዚህ ተቋማትና ግለሰቦች በድርጅቱ ስም አክብሮቴን መግለፅ እወዳለሁ፡፡

የሞራል ከፍታን እስከያዝን ድረስ፤ እንደአገር መከታ ጠባቂ እሰከሆንን ድረስ ውድመት በግንባታ ይተካል፤ ድህነት በልማት ይሸነፋል፤ ሀዘንም ወደ ደስታ ይቀየራል፡፡ አመልድ ኢትዮጵያ በራሱ ንብረት ላይ የደረሰበትን ውድመት ብቻ ሣይሆን በሚያገለግለው ህብረተሰብም የደረሰውን ኢኮኖሚያናዊና ማህበራዊ ውድመት በልማት ለመተካት ከፍተኛ ርብርብ እያደረገ ይገኛል፡፡ በዚሁ አጋጣሚ ጥረቱን አጠናክሮ እንደሚቀጥል እያረጋገጥን፤ በድጋሜ ለታማኝና ጀግና ሠራተኞቻችን ያለኝን አድናቆት ስገልፅ ታላቅ ክብር እየተሰማኝ ነው፡፡

ቅኖችና ታማኞች ዓለምን ይቀይራሉ!!

     አመሰግናለሁ፡፡

 

 

Copyright © 2012 ORDA Ethiopia.
All Rights Reserved.