የ2016 ዕቅድ አፈጻጸም ግምገማና የ2017 ዕቅድ ትውውቅ ተካሄደ
በአማራ ክልል በሚከናወኑ ዘርፈ-ብዙ የልማት ስራዎች ጉልህ አሻራ ያለው ህዝባዊ የልማት ተቋም ነው፤ አመልድ፡፡ ድርጅቱ የ2016 ዕቅድ አፈጻጸም ግምገማና የ2017 ዕቅድ ትውውቅ ከሚያዝያ 2-4/2009 ዓ.ም በባህር ዳር ግራንድ ሪሶርትና ስፓ አካሂዷል፡፡
ድርጅቱ 11ኛውን ጠቅላላ ጉባኤ በድምቀት ባከበረበት ወቅት ቀርቦ የጸደቀው ያለፉት 3 ዓመታት (2014-2016) ሪፖርት ለሰራተኛው የቀረበ ሲሆን የአመልድ ጠቅላላ ጉባኤ ያፀደቃቸውን ዕቅዶች፤ የሥራ አመራር ቦርዱ በየጊዜው በዕቅድ አፈፃፀም ግምገማ ወቅት ያስቀመጣቸውን አቅጣጫዎች ከወቅታዊ ሁኔታዎች ጋር በማጣጣምና የልማት ሀብት በማፈላለግ የልማት ሥራዎች ሲከናወኑ ቆይተዋል፡፡
በተለይም ደግሞ እ.ኤ.አ 2016 ድርጅቱ ወደ ከፍተኛ የዕድገት ምዕራፍ የተሸጋገረበት የስኬት አመት ነበር፡፡ ይህ ዓመት ከሁለት ቢሊዮን ብር በላይ የኘሮጀክት ማስፈፀሚያ በጀት የተገኘበት የሶሻልA ኢንተርኘራይዝ የማቋቋም ተግባር የተጀመረበት እና አመልድ በአገር-አቀፍና በዓለም-አቀፍ ደረጃ ሽልማትና ዕውቅና ያገኘበት ዓመት ነበር፡፡
ሪፖርቱ የቁልፍና አበይት ተግባራት አፈጻጸም እንዲሁም የሶሻል ኢንተርፕራዝ ልማት አፈፃፀም በዝርዝር ቀርቧል፡፡ የ2016 ውጭ ኦዲተር የፋይናንስ ህጋዊነት ምርመራ “እንከን የለሽ (Unqualified)” ውጤት የተገኘ ሲሆን ይህም የድርጅቱን የፋይናንስ አስተዳደር ጥንካሬ ያመለክታል፡፡
ከዚህ ባሻገር አመልድ በክልሉ መንግስት ሊሰፉ የሚችሉ ምርጥ ተሞክሮዎች ያሉት ሲሆን
-
- የማህበረሰብ አቀፍ ደን ልማት (Community Based Greening Programe)
- ተሳትፏዊ የደን አስተዳደር (Participatory Forest management)
- ሁሉን አቀፍ የመሬት አያያዝና አስተዳደር አሰራር (Comprehensive Land Husbandry Approach)
- የሃብት (የኑሮ) ደረጃን መሰረት ያደረገ የተጠቃሚ ልየታና ድጋፍ
- በፀሐይ ሃይል የሚሰራ አምፖል (solar lantern)
- ቤተሰብና በማህበረሰብ ደረጃ የዉሃ ማቆር ኩሬዎችን (household and community ponds) ማስፋፋት
- ማህበረሰብ አቀፍ የመጠጥ ወሃና ስነ-ንጽህና ፕሮጀክት (Community managed Project)
- በቤተሰብ ደረጃ የስርዓተ-ጾታ ትንተና (Gender Household Analysis) ማካሄድ ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡
አመልድ የ2017 ዕቅድ በዝርዝር የቀረበ ሲሆን ተሳታፊዎች ጥያቄዎችንና ዕቅዱ እንዲዳብር የሚረዱ አስተያየቶችን ያቀረቡ ሲሆን በቀጣይ ትኩረት የሚሹ ጉዳዮችና አቅጣጫዎች የንቅናቄ ዕቅድ ቀርቦ ለተፈጻሚነቱ ሁሉም ርብርብ እንደሚያደርግ ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡