"ነባር ደኖችን በመጠበቅ እና አዳዲስ ተከላ በማካሄድ ለብዝሃ-ህይዎት መሻሻል እየሰራን ነው!”፣ አለማየሁ ዋሴ (ፒኤች.ዲ.)
አመልድ ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ በ2023 ከሚተገብራቸው 38 ፕሮጀክቶች መካከል የቤተክርስቲያን ደንን መሰረት ያደረገ የመልክዓ-ምድር መልሶ ማልማት ፕሮጀክት አንዱ ነው፡፡ ፕሮጀክቱ በደቡብ ጎንደር ዞን ደራ ወረዳ እና እስቴ ወረዳ እየተተገበረ ይገኛል፡፡ የአመልድ ኢትዮጵያ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር አለማየሁ ዋሴ የፕሮጀክቱን እንቅስቃሴ በጎበኙበት ወቅት እንዳሉት ከ100 ዓመታት በፊት 40% የነበረው የደን ሽፋን ወደ 4 በመቶ ዝቅ ብሏል፡፡ በመሆኑም አጭር የዝናብ ወቅት፣ የብዛ-ህይዎት መዛባት እና ለአየር ንብረት ለውጥ ተጋላጭ ሆነናል ብለዋል፡፡
ዋና ዳይረክተሩ አክለውም አመልድ ኢትዮጵያ ነባር ደኖችን በመጠበቅ እና አዳዲስ ተከላ በማካሄድ ለብዝሃ-ህይዎት መሻሻል እየሰራን ነው ፡፡ ለአብነትም የቤተ-ክርስቲያን ደኖች ከዚህ በፊት የአንድ ትልቅ ደን አካል የነበሩ በመሆናቸው በተከላ በማጠናከር እና ዙሪያቸውን በድንጋይ በማጠር፣የወል መሬቶች ላይ ተከላ በማካሄድ እና ከእንስሳት ንክኪ ነጻ በማድረግ አንዱን ከአንዱ በማገናኘት የአካባቢ ደህንነትን እና የደን ሽፋንን ለመጨመር እየሰራን ነው ብለዋል፡፡ እንዲሁም ከደን ውጤቶች ጋር ኑሯቸውን የመሰረቱ አርሶ አደሮችን በንብ ማነብ፣ በበግ እርባታ እና በዶሮ እርባታ እንዲሰማሩ በማድረግ የደን ጭፍጨፋን ለመቀነስ እየሰራን ነው ብለዋል፡፡ በተጨማሪም የአካባቢው ወጣቶች ማገዶ ቆጣቢ ምድጃ እንዲያምርቱ እና ለአካባቢው በመተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያቀርቡ ተደርጓል፡፡
አመልድ ኢትዮጵያ በ2015 ዓ.ም ክረምት በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች በሚተገበሩ ፕሮጀክቶች አማካኝነት የአካባቢ ደህንነትን እና የደን ሽፋንን ለመጨመር የሚያግዙ እንዲሁም ኢኮኖሚያዊ ጥቅም የሚሰጡ 6.8 ሚሊዮን ችግኞች ተከላ እያካሄደ ነው፡፡