ሁለተኛው ዙርን የተቀናጀ የአስቸኳይ ጊዜ የእለት ደራሽ እርዳታ ፕሮግራም (JEOP 2.0) ለመተግበር ስምምነት ተፈረመ፤
በአማራ ክልል በተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ ችግሮች በሚከሰቱ ድንገተኛ አደጋዎች ምክንያት የሚፈጥሩ ጉዳቶችን /የሰዎችን ህይወት ለመታደግ እና ሀብት ንብረታቸውን እዳይሟጠጥ ለማድረግ/ አመልድ ኢትዮጵያ በካቶሊክ እርዳታ ድርጅት ጋር በመተባበር ከአሜሪካን ህዝብ እና መንግስት /USAID/ በሚያገኘዉ ድጋፍ ላለፉት በርካታ አመታት የመጀመሪያውን ዙር የተቀናጀ አስቸኳይ ጊዜ እርዳታ ፕሮግራም በሰሜን ወሎ እና ዋግ-ኸምራ በሚገኙ 15 ወረዳዎች እየተተገበረ መሆኑ ይታወቃል፡፡
አሁንም ለሁለተኛ ጊዜ ከአሜሪካ አለም አቀፍ ተራድኦ ድርጅት በተገኘ ድጋፍ ለቀጣይ አምስት ዓመታት ማለትም እ.ኤ.አ ከግንቦት 2023 እስከ ሚያዝያ 2027 የሚቆይ ሁለተኛው ዙር የአስቸኳይ ጊዜ የምግብ እርዳታ በሰሜን ወሎ ዞን በሚገኙ 11 ወረዳዎች እና በዋግ-ኸምራ ዞን ውስጥ በሚገኙ አራት ወረዳዎች በቀጣይ ድጋፍ ለማድረግ በአመልድ ኢትዮጵያ እና በካቶሊክ እርዳታ ድርጅት መካከል የፕሮጀክት ሰምምነት ተፈርሟል፡፡
በስምነቱም ወቅት የአመልድ ኢትዮጵያ ዋና ዳይሬክተር ዓለማየሁ ዋሴ (ፒኤች.ዲ.) እንደገለፁት ስምምነቱ በክልላችን በተጠቀሱት 15 ወረዳዎች ለሚገኙ በተፍጥሮ እና ሰው ሰራሽ ምክንያት ሊደርሱ የሚችሉትን ድንገተኛ ጉዳቶች ለመታደግ ዘርፈ ብዙ ጥቅም እንዳለው ገልፀዋል። ዋና ዳይሬክተሩ በአሜሪካ ተራዳኦ ድርጅት ሊደረግ ለታሰበው ሁለተኛ ዙር የአስቸኳይ ምላሽ ፕሮግራም ከፍተኛ ምስጋና አቅርበዋል፡፡ ፕሮግራሙ እ.ኤ.አ ከሐምሌ 2012 ጀምሮ ሲካሄድ የቆየ እና በክልላችን በተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ ችግሮች ምክንያት እንዲሁም በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል በቅርቡ በነበረው ጦርነት ምክንያት ተፈናቅለው እና ጉዳት ለደረሰባቸው ማህበረሰቦች ህይወት ሲታደግ መቆቱን አውስተዋል፡፡
በፕጀክቱ ስምምነት መሰረት የመጀመሪያው በጀት ዓመት በምግብ እህል/ዘይት 50,833.5 ሜትሪክ ቶን (44,985 ሜ.ቶ ስንዴ፣ 4,498.5 ሜ.ቶ ክክ፣ 1,350 ሜ.ቶ የምግብ ዘይት) ድጋፍ የሚደረግ መሆኑን እና ለእርዳታ እህሉ ማጓጓዣ እና ሌሎች ተያያዥ ወጭዎች የሚውል 8,093.407 ዶላር በጀት መመደቡን በስምምነቱ ላይ ተጠቅሷል፡፡