አሳታፊ እና የተቀናጀ የመሬት አጠቃቀም ዕቅድ ፕሮጀክት ትውውቅ ተካሄደ
የማንኛውም ሀገር የገጠር እና የከተማ ማህበረሰብ የኑሮ ሁኔታ እና ማህበራዊ ውህደት የተመሰረተው የተፈጥሮ ሀብቶችን በተለይም መሬትን በአግባቡ በመቀጠም ላይ ነው፡፡ ሆኖም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የእነዚህ የተፈጥሮ ሀብቶች ከመጠን በላይ መጠቀም የተፈጥሮ ሀብት መሟጠጥን፣ የብዝሀ ሕይወት መጥፋትን፣ የመሬት ግጭቶችን እና የውስጥ መፈናቀልን በተለይም እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ታዳጊ አገራት ውስጥ እየፈጠረ ይገኛል፡፡ እንደ የህዝብ ብዛት፣ የከተማ ልማት/መስፋፋት፣ የመሬት እና የውሃ ሀብቶች አላግባብ መጠቀም እንዲሁም ትክክለኛ የመሬት አጠቃቀም እቅዶችን ለመተግበር በቂ ዕውቀት እና ቴክኒካዊ አቅም አለመኖር ችግሩን እያባባሱ ይገኛሉ ፡፡ ከሁኔታው ከባድነት አንጻር ሲታይ አሳታፊ እና የተቀናጀ የመሬት አጠቃቀምን በተመለከተ ስኬታማ ዕቅድ ማውጣትና መተግበር እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡
በአካባቢው ላይ ተፅዕኖ የማያደርሱ የአዝዕርትና የዕፅዋት ዝርያዎችን በማልማትና የደን ሃብትን በማሳደግ የመሬት አጠቃቅምና አያያዝ ጥናቱ በሚወስነው መሰረት ተግባራዊ እንዲሆን በማድረግ ተግባራዊነቱን መከታተል፤ በወል መሬቶች ላይ እየደረሰ ያለውን ወረራና ጉዳት እንዲሁም የአጠቃቀም ችግር በመከላከል የእንስሳት መኖ ምርትን ማሳደግና ዘላቂነቱን ማስጠበቅ፤ ምርትና ምርታማነትን የሚጨምሩ የመሬት አጠቃቅም ስርዓቶችን ማስፋፋት እና ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና አካባቢያዊ ልማትን ማፋጠን፤ የመሬትን የማምረት አቅም ያገናዘበ የመሬት አጠቃቅምና አያያዝ እቅድ ተግባራዊ እንዲሆን በማድረግ የመሬትን ዘላቂነት አስጠብቆ ለቀጣዩ ትዉልድ ማስተላለፍ ጊዜ የማይሰጣቸው ተግባራት ናቸው፡፡
በመሆኑም የተዛባ የመሬት አጠቃቅም ስርዓት በማሻሻል ዘላቂነት ያለው የመሬት አጠቃቅምና አያያዝ ስርዓት በመዘርጋት ስነ-ምህዳሩን በጠበቀ መልኩ ዘላቂነት ያለው ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የህብረተሰቡን አኗኗር ማሻሻል እንዲሁም የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ስራዎች በመሬት አጠቃቅምና አያያዝ እቅድ ጥናት ላይ ተመስርተው ተግባራዊ እንዲሆኑ በማድረግና ዘላቂነታቸውን በማረጋገጥ ዘላቂ ልማት እንዲመጣ ማስቻል ከምንጊዜውም በላይ ወሳኝ ነው፡