Print

አመልድ ለህብረተሰቡ የገነባቸውን ንፁህ የመጠጥ ውሃ ተቋማት አስመረቀ

በታደሰ ዘበአማን

(መጋቢት 12፣ 2008-ባህርዳር) አመልድ ኤ ግሊመር ኦፍ ሆፕ ከሚባል የረጅ ድርጅት፣ ከመንግስት፣ ከአልማ፣ ከአብቁተና ከማህበረሰቡ ጋር በመተባበር እየፈፀመ በሚገኘው የተቀናጀ የማህበረሰብ ልማት ፕሮጀክት ውስጥ በመጀመሪያው ምዕራፍ የገነባቸውን 11 መለስተኛ ጥልቅ የመጠጥ ውሃ ጉድጓዶችን መጋቢት 04/2008 ዓ.ም አስመረቀ፡፡ የመጠጥ ውሃ ጉድጓዶቹም በጎንደር ዙሪያ ወረዳ በሚገኙ 5 የገጠር ቀበሌዎች ውስጥ ለሚገኙ  4718 ሰዎች (49 በመቶ ሴቶች) ጥቅም እንዲሰጡ ሆነው ነው የተገነቡት፡፡

                          glimmer (1)

አመልድ የበለፀገ የአማራ ክልል ህዝብ ተፈጥሮ የማየት ራዕዩን ለማሳካት ባለፉት 31 ዓመታት ከተለያዩ ረጅ ድርጅቶች፣ መያዶች፣ መንግስትና ማህበረሰቡ ጋር በመተባበር ሰፊ ርብርብ በማድረግ ላይ የሚገኝ የአማራ ክልል ህዝብ የልማት አቅም ነው፡፡ እ.ኤ.አ በ2015 ዓ.ም ብቻ 27 ከሚሆኑ የረጅ ድርጅቶች  ጋር በመተባበር 62 የተለያዩ ፕሮጀክቶችን በመፈፀም 1.69 ሚሊዮን የሚሆኑ የክልሉን ህዝቦች ተጠቃሚ አድርጓል፡፡ ከላይ የተገለፀው የተቀናጀ የማህበረሰብ ልማት ፕሮጀክቱም አንዱ ነው፤ ፕሮጀክቱም የሚፈፀመውም በአልማ፣ በአመልድና በአብቁተ የሶስትዮሽ ትብብር ሲሆን፡፡ እነዚህ ድርጅቶች በፕሮጀክቱ ውስጥ ያላቸው ድርሻ የተለያየ ሲሆን የአመልድ ድርሻ ንፁህ የመጠጥ ውሃ ማበልፀግና በማህበረሰቡ የግልና የአካባቢ ንፅህና ልምዱ ዙሪያ ለውጥ የሚያመጡ ስራዎችን ማከናወን ነው፡፡

ከ11 የውሃ ተቃማት መካከል አንዱ በሆነው ገዛው ቁጥር አንድ የመለስተኛ ጥልቅ ጉድጓድ ውሃ ተጠቃሚና የውሃ ኮሚቴ ሊቀመንበር የሆኑት ወ/ሮ አደይ ስንቴ የተባሉት ግለሰብ ውሃው በመሰራቱ ያገኙትን ጥቅም ሲያስረዱ፣  ይህ ውሃ እንዲህ አምሮ በአመልድና በእኛ ትብብር ከመስራቱ በፊት ራቅ ብሎ ከሚገኝ ወንዝ ከውሻ፣ ከአህያና ከሌሎችም እንስሳት ጋር በመሻማት የሚቀዱት ውሃ ንፅህና የሌለው ስለነበር እነሱም ሆነ ልጆቻቸው በከፍተኛ ደረጃ በውሃ ወለድ በሽታዎች ተጠቂ  እንዲሆኑ አድርጓቸው እንደነበር ገልፀዋል፡፡ አሁን ግን እግዚአብሄር ይመስገንና የምንጠቀመው ውሃ ንጹህ ስለሆነ በሽታ ቀንሶልናል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

የውሃ ተቋማቱ በዘላቂነት አገልግሎት እንዲሰጡ የተለያዩ ስራዎች ተሰርተዋል፡፡ ለምሳሌ የውሃ ተቋማቱን በበላይነት የሚያስተዳድሩዋቸው  55 የውሃ ኮሚቴዎችና 22 ጠጋኞች ተዋቅረው አስፈላጊው ስልጠናም ተሰጥቷቸዋል፡፡ ሁሉም የውሃ ተቋማትም ውሃው ቢበላሽ ማሰጠገኛ የሚሆን ከብር 3000 እስከ ብር 6120 በመቆጠብ በድምሩ ብር 45000 በላይ የሆነ ገንዘብ በአማራ ብድርና ቁጠባ ተቋም አስቀምጠዋል፡፡ በየወሩም አምስት አምስት ብር እያስቀመጡ ይገኛሉ፡፡

                          glimmer (2)

ፕሮጀክቱ የተጠቃሚዎችን የአካባቢና የግል ንፅህና ለማሻሻል ለ4705 ሰዎች አገልግሎት የሚሰጡ የመጸዳጃ ቤቶች እንዲገነቡ አግዟል፡፡ እንዲሁም ለ22 የመንደር ጤና አስተማሪዎችና ለ10 የጤና ኤክስቴንሽን ሰራተኞች ስልጠና ተሰጥቷል፡፡

እነዚህን ስራዎች ለመስራት  ከ ኤ ግሊመር ኦፍ ሆፕ ብር 3.5 ሚሊዪን ብር፣ ከህብረተሰቡ 321810 ብርና ከአመልድ ደግሞ ብር 262785 በድምሩ ብር 4.14 ሚሊዪን ገንዘብ ጥቅም ላይ ወሏል፡፡

የተመረቁት የመጠጥ ውሃ ተቋማት በአግባቡ የተገነቡ፣ የታጠሩና አስፈላጊው ሁሉ እንክብካቤ የተደረገላቸው በመሆኑ ለሌሎች ስራዎችም አርአያ እንደሆኑ የረጅ ድርጅቱ የኢትዮጵያ ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ገ/ህይወት አበበ በምረቃ ስነስርአቱ ወቅት ገልፀዋል፡፡ እንዲሁም አቶ ገ/ሕይወት አያይዘውም ህብረተሰቡ የተገነቡለትን ተቋማት ለረጅም ጊዜ መጠቀም እንዲችል በእንክብካቤ እንዲይዛቸው አሳስበዋል፡፡