የቤተሰቡን ኑሮ የቀየረው ወጣት ዋለልኝ
ወጣት ዋለልኝ ብሩ በሰሜን ወሎ ዞን ጉባላፍቶ ወረዳ 023 ውድመን ቀበሌ ነዋሪ ነው፡፡ የ27 ዓመት ወጣት ሲሆን ትዳር አልመሰረትም፡፡ ወላጅ አባቱን በ16 ዓመቱ በሞት ያጣ ሲሆን ቀሪ ታናሽ እህት እና ወንደሞቹን የማሳደግ እና የማስተማር ኃላፊነት የወደቀው ገና በጥዋቱ በልጅነት ትክሻው ላይ ነበር፡፡ በዚህም የ9ኛ ክፍል ትምህርቱን አቋርጦ በግብርና ስራ ተሰማራ፡፡ ነገር ግን ቤሰተቡ ምንም ሃብት ስላለነበራቸው ስራ ለመጀመር ተቸግሮ ነበር፡፡ ኑሯቸውም ከእጅ ወደ አፍ የሆነ እና የተጎሳቆለ ነበር፡፡
በአመልድ ኢትዮጵያ ለአደጋ የማይበገር የኑሮ ማሻሻያ ፕሮጀክት በአማራ ክልል 7 ወረዳዎች (ወልድያ ክላስተር 3 ወረዳዎች - ራያ ቆቦ፣ ሃብሩ እና ጉባ ላፍቶ)፣ መቄት ክላስተር 2 ወረዳዎች (መቄት እና ዋድላ) እና መሃል ሜዳ ክላስተር 2 ወረዳዎች (መንዝ ማማ ምድር እና መንዝ ጌራ ምድር) 36,000 ቤተሰቦችን በምግብ ዋስትና እራሳቸውን እንዲችሉ በማድረግ ከተረጅነት እንዲወጡ እየሰራ ይገኛል። የወጣት ዋለልኝ ቤተሰቦችም በምግብ ራሳቸውን ያልቻሉ ስለነበሩ በፕሮጀከቱ ታቅፎ ለቤተሰቡ ኑሮ መሻሻል ምክንያት ሁኗል፡፡
ፕሮጀክቱ እንደጀመረ በመንደር ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ቁጠባ አባል በመሆን ስለገንዘብ አያያዝ እና አጠቃቀም እና ስለበሬ ማድለብ ስልጠና አግኝቷል፡፡ በመሆኑም ከ3 ዓመት በፊት 15,000 ብር ከፋይናንስ ተቋማት በመበደር 2 በሬ በማድለብ ጀመረ፡፡ በዓመቱ ካፒታሉን ወደ 50,000 ብር አሳደገው፡፡ በ2ኛው ዓመት 30,000 ብር ተበድሮ በሬ በማድለብ ባገኘው ጠቀም ያለ ገቢ የሳር ቤታቸውን አፍርሶ ወደ ቆርቆሮ ቤት ቀየረው፡፡ በ3ኛው ዓመት 40,000 ብር ተበድሮ በሬ በማድለብ የተሻለ ገቢ አገኘ፡፡ በወቅቱም በ30,000 ብር ከሚጦ ከተማ ቦታ ገዛ ( ቦታው አሁን ካርታና ፕላን ያለው ሲሆን 350,000 ብር ይሸጣል)፡፡ በአሁኑ ሰዓት 2 በሬዎችን እያደለበ ነው፤ እንዲሁም አንድ የአሜሪካ ዝርያ ላም አለችው፡፡
"አሁን አጠቃላይ ካፒታሌ ከ30,000 ብር ብድረ ተለስቼ እስከ 800,000 ብር ደርሷል፡፡ ለዚህ ለውጥ የበቃሁት ደግሞ ፕሮጀክቱ ባደረግልኝ ድጋፍ በተለይም ስለበሬ ማድለብ የሰጠኝ ስልጠና ቀይሮኛል፡፡ ከዚህ በፊት ስልጠና ሳላገኝ በሬ ለማድለብ ሞክሬ በአንድ ጊዜ ብዙ ፉርሽካ ስለመገብሁት አንድ በሬ ሆዱ ተነፍቶ ሙቶብኛል" ብሏል፡፡
"በአጠቃላይ የተሰጠኝ የከብት ማድለብ ስልጠናው ጠቅሞኛል፡፡ የደለበ በሬ መቼ በጥሩ ዋጋ እንደሚሸጥ አውቃለሁ፡፡ ብዙ ጊዜ ሰዎች አድልበው የሚሸጡት የበዓል ወቅት ነው፡፡ በመሆኑም በበዓል ወቅት ርካሽ ስለሚሆን የማደልበውን በሬ የምገዛው በበዓል ጊዜ ነው፡፡ የምሸጠው ደግሞ ወልዲያ ያሉ ታዋቂ ስጋቤቶች ጋር የገበያ ትስስር ፈጥሬ ነው፡፡ በመሆኑም በተሻለ ዋጋ እሸጣቸዋለሁ፡፡"
ወጣት ዋለልኝ ከዚህ በኋላ የበሬ ማድለብ ስራውን በማስፋት ብዙ በሬዎችን በተለያየ ዙር ለማድለብ እቅድ አለው፡፡ የማድለቢያ ቦታ እና ጠቀም ያለ የብር ብድር አቅርቦት እንደሚፈልግ ተናግሯል፡፡
ላለፉት 6 ዓመታት 36,186 (ሴት፡ 11,119) ቤተሰቦች በመንደር ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ቁጠባ በመደራጀት $1.22 ሚሊዮን በፕሮጀክቱ አማካኝነት ቆጥበዋል። እንዲሁም 27,544 (ሴት፡ 10,530) ቤተሰቦች በተመረጡ እሴት ሰንሰለቶች ተሳትፈዋል፤ 33,452 ቤተሰቦች (ሴት፡ 15,153) በተጓዳኝ ስራዎች በመሰማራት ተጨማሪ የገቢ ምንጭ አግኝተዋል።