በአመልድ ኢትዮጵያ የሴቶችን ፖለቲካዊ ተሳትፎ በማብቃት የአመራር እና ዉሳኔ ሰጭነት አቅም ማሻሻል ፕሮጀክት የመዝጊያ አውደ-ጥናት ተካሄደ፡፡
አመልድ ኢትዮጵያ ከሲቪል ሶሳይቲ ሳፖርት ፕሮግራም በተገኘ የገንዝብ ድጋፍ ለ28 ወራት በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ምዕራብ በለሳ ወረዳ በተመረጡ 15 ቀበሌዎች የሴቶችን ፖለቲካዊ ተሳትፎ በማብቃት የአመራር እና ዉሳኔ ሰጭነት አቅም ለማሻሻል ሲተገብር የቆየውን ፕሮጀክት አጠናቀቀ፡፡
ፐሮጀክቱ በ15 ቀበሌዎች 75 የውይይት ቡድን በማቋቋም ህብረተሰቡን በተለይ ደግሞ ሴቶችን ያሳተፈ ፕሮጀክት ሲተገብር ቆይቷል፡፡ፕሮጀክቱ በሦስት አመታት በቆየበት ወቅት ለ1ሺህ 121(ሴ፡ 498) ስልጠና ተሰጥቷል፡፡ በፕሮጀክቱ በተደረገው ስልጠና 36 ሴቶች በተለያዩ የቀበሌ እና የወረዳ የአመራር እና ዉሳኔ ሰጭ ቦታዎች ላይ እንዲወከሉ ተደርጓል፡፡
የአመልድ ኢትዮጵያ የስርዓተ ጾታ፣አካል ጉዳተኞች እና ወጣቶች የሥራ እድል ፈጠራ ፕሮግራም ማኔጀር ወ/ሮ ዮርዳኖስ ድረስ የፕሮጀክቱን መጠናቀቅ አስመልክቶ እንደተናገሩት ፕሮጀክቱ የሴቶችን ውሳኔ ሰጭነት እና ፖለቲካዊ ተሳትፎ ለማሳደግ የአቅም ግንባታ ስልጠና በሴቶች መብት ላይ ለሚሰሩ ተቋማት፣ የሐይማኖት አባቶች፣ የሐገር ሽማግሌዎች እና የማህበረሰብ አመቻቾች አባላት ስልጠና ተሰጥቷል ብለዋል፡፡
ወ/ሮ ዮርዳኖስ አያይዘው ፕሮጀክቱ የሴቶችን ፖለቲካዊ ተሳትፎ እና አመራር ሰጭነት እንዲሻሻል እና የአስተሳሰብ ለውጥ እንዲመጣ ትልቅ ሚና ተጫውቷል ብለዋል፡፡ በተለይም ፕሮጀክቱ ለማህበረሰብ አመቻቾች ስልጠና በመስጠት የሰለጠኑት ደግሞ ሌሎች አባላትን እንዲያወያዩ በማድረግ የሴቶች ፖለቲካዊ ተሳትፎ እንዲያድግ፣ጎጅ ልማዳዊ ድርጊት እንዲቀረፍ እና በቤት ውስጥ የሴቶች የስራ ጫና እንዲቀንስ ትልቅ ሚና ተጫውቷል ብለዋል፡፡
በፕሮጀክት ማጠናቀቂያ እለት የፕሮጀከቱ ተጠቀሚ የማህበረሰብ አባላት መካከል ከምዕራብ በለሳ ወረዳ የብርብራክ ቀበሌ ነዋሪ ቄስ መሠረት ነጋ እና የአሽከር ተራራ ቀበሌ ነዋሪ ወ/ሮ ማሪቱ አሻግሬ እንዳሉት በቀበሌያቸው የሴቶች ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ እኩልነት እና መብት የተሻሻለ መሆኑን እና ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች መቀነሳቸውን (ማለትም ያለዕደሜ ጋብቻ እና አላስፈላጊ ድግስ መቀነሱን) ተናግረዋል፡፡ ተጠቃሚዎች አያይዘው ሴቶች ወሳኔ ሰጪ በሆኑ ቦታዎች በፍርድ ሸንጎ፣በቅሬታ ሰሚ እና በቀበሌ አመራር ቦታዎች ላይ ተሳትፎ በማድረግ ተጠቃሚነታቸው እየተረጋገጠ መምጣቱን ገልጸዋል ::
የምዕራብ በለሳ ወረዳ የሴቶች እና ሕፃናት ጉዳይ ጽ/ቤት ተወካይ አቶ በሪሁን አስማረ በፕሮጀክት ርክክቡ ወቀት እንደተናገሩት አመልድ ኢትዮጵያ መሰረቱን ስለፈጠረልን የሴቶችን ፖለቲካዊ ተሳትፎ እና አመራር ሰጭነት ፕሮጀክት ተረክበን እናስቀጥላለን ብለዋል፡፡በመጨረሻም ታሳታፊዎቹ ፕሮጀክቱ መብታችንን ለማስከበር ከፍተኛ ግንዛቤ የፈጠረልን ስለሆነ አጠናክረን እናስቀጥለዋለን ብለዋል፡፡