የሴቶችን የፖለቲካ ተሳትፎ፣ የአመራር እና ውሳኔ ሰጭነት ማሳደግ የሚያስችል አውደ-ጥናት ተካሄደ፡፡
አመልድ ኢትዮጵያ የሴቶችን የፖለቲካ ተሳትፎ በማብቃት የመሪነት እና የውሳኔ ሰጭነት አቅማቸውን ለማጎልበት በምዕራብ በለሳ እና በእነብሴ ሳር ምድር ወረዳዎች ፕሮጀክት ቀርጾ ተግባራዊ እያደረገ ይገኛል፡፡ በዚህም አመልድ ኢትዮጵያ እና አለም ብርሃን ከባሕር ዳር ዩኒቨርስቲ ጋር በመተባበር የሴቶችን የፖለቲካ ተሳትፎ፣ አመራርና ውሳኔ ሰጭነት የተመለከቱ ፖሊሲዎችን፣ህጎችን እና አሠራሮችን የሚተነትን እና የሚያሳይ ዐውደ-ጥናት መጋቢት 18/2015 ዓ.ም በባሕር ዳር ከተማ አካሂደዋል፡፡
የአመልድ ኢትዮጵያ ም/ዋና ዳይሬክተር /የሐብት አስተዳደር/ ሽብሬ ጆርጋ (ፒኤች.ዲ.) አውደ ጥናቱን ሲከፍቱ እንደተናገሩት ሴቶች የፖለቲካ መሪነቱን ካረጋገጡ በኢኮኖሚ እና በማኀበራዊ መስኮች ለመሳተፍ እድል እንዲያገኙ ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል ብለዋል፡፡ ወ/ሮ ሽብሬ አያይዘውም ሴቶች ከቁጥር እና ከውክልና ማሟያ ባለፈ በውሳኔ ሰጭነት ላይ ሚና ሊኖራቸው ይገባል ብለዋል፡፡
በወርክ ሾፑ ላይ ከባሕር ዳር ዩኒቨርስቲ የጥናት ጽሁፍ አቅራቢ ዶ/ር መሠረት ዘወዱ እንደገለጹት በፖሊሲዎች እና በሕጎች ላይ አስገዳጅ ሕግ አለመኖር የሴቶችን የፖለቲካ ተሳትፎ እና የዉሳኔ ሰጭነት እድገት ላይ እንቅፋት የፈጠረ በመሆኑ ሊሻሻል ይገባል ብለዋል፡፡
በአውደ ጥናቱ ከአማራ ክልል ምክር ቤት፣ ከሴቶች ጉዳይ ቢሮ፣ ከፍትሕ ቢሮ፣ ከምዕራብ በለሳ እና እነብሴ ሳር ምድር መወረዳዎች የመንግሥት መስሪያ ቤት ተወካዮች ተሳትፈዋል::