Joomla TemplatesBest Web HostingBest Joomla Hosting

Home ዜና የቅርብ ዜናዎች ምርታማ የበግ እና የሰብል ዝርያዎች ለአርሶ አደሮች ኑሮ መሻሻል

   ምርታማ የበግ እና የሰብል ዝርያዎች ለአርሶ አደሮች ኑሮ መሻሻል

    sheep breed and crop varieties

አርሶ አደር ገዳሙ ባለው ግማሽ ሄክታር ማሳ በግብርና ስራ ኑሮውን ለማሸነፍ ቢታትርም የቤተሰቡን የምግብ ፍጆታ በበቂ ሁኔታ አያገኝም፡፡ በዚህም ተጨማሪ የእርሻ ማሳ በመከራየት ቤተሰቡን ለመምራት ይጥራል፡፡ እንዲሁም ኑሮውን ለመደጎም ከእርሻ ሥራ በተጨማሪ በግ ያረባል፡፡

ገዳሙ ጌቴ በእናርጅ እና እናውጋ ወረዳ የጎሳ ቀበሌ ነዋሪ ሲሆን 42 ዓመት ጎልማሳ እና የአራት ልጆች አባት ነው፡፡ የእናርጅ እና እናውጋ ወረዳ ምርታማ ቢሆንም ከፍተኛ የህዝብ አሰፋፈር ጥግግት ያለበት በመሆኑ የአርሶ አደሮች የእርሻ ማሳ የተበጣጠሰ እና አነስተኛ ነው፡፡ አርሶ አደር ገዳሙም 0.5 ሄክታር ማሳ ብቻ ነው ያለው፤ በዚህም ተጨማሪ 1.025 ሄክታር ማሳ ከሌሎች አርሶ አደሮች ተከራይቶ ያርሳል፡፡ ነገር ግን የመሬት ኪራይ ውድ በመሆኑ የግብርና ሥራው ውኃ ቅዳ ውኃ መልስ ሆኖበት ቆይቷል፡፡

አርሶ አደር ገዳሙ ኑሮውን ለማሸነፍ ከግብርና ሥራው በተጨማሪ በግ እያረባ ሲጠቀም ኑሯል፡፡ ነገር ግን የበጎች ዘር ምርታማ ስላልነበሩ የሚጠበቀውን ያህል ተጠቃሚ አልነበረም፡፡ በአመልድ ኢትዮጵያ ግብርናን ከተፈጥሮ ሃብት እንክብካቤ እና ከስነ-ምግብ ፕላስ ጋር የማስተባበር ፕሮጀክት በምስራቅ ጎጃም ዞን ሁለት ወረዳዎች ማለትም በጎንቻ ሲሶ እነሴ ወረዳ እና እናርጅ እናውጋ ወረዳ በስነ-ምግብ እና ስነ-ፅዳት ዙሪያ ተጠቃሚዎች የባህሪ ለውጥ እና መሻሻል እንዲያመጡ ሥራ ሲጀምር እርሱም የፕሮጀክቱ ተጠቃሚ ሆነ፡፡

     sheep breed and crop varieties 1

ከፕሮጀክቱ ምርታማ የሆነ የዋሸራ አውራ በግ በማግኘቱ በጎቹ አሁን 3 ምርታማ ጠቦቶችን ወልደውለታል፡፡ የተወለዱት ጠቦቶች አካላቸው ረዣዥሞች እና ቀለማቸው በገበያ ተፈላጊ በመሆኑ ትልቅ ተስፋ ሰንቋል፡፡ አቶ ገዳሙ እንዳሉት የዋሸራ አውራው በአካባቢው ላሉ አርሶ አደሮች 55 በላይ በሥጋቸው ምርታማ ጠቦቶችን ወልዶላቸዋል፡፡ ፕሮጀክቱ በአጠቃላይ 100 ምርታማ የዋሸራ አውራ በግ ለተጠቃሚዎች በመስጠቱ 839 ጠቦቶች ተወልደዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ አርሶ አደር ገዳሙ ምርታማ የሆነ ምርጥ የስንዴ ዘር ከፕሮጀክቱ በማግኘቱ የጥማድ ግማሽ ማሳው ላይ ዘርቶ ጥሩ ውጤት እያገኘበት መሆኑን ተናገሯል፡፡

ፕሮጀክቱ በምስራቅ ጎጃም ዞን ሁለት ወረዳዎች ማለትም በጎንቻ ሲሶ እነሴ ወረዳ 3 ቀበሌዎች (ደብረ ሃይል፣የቡቻር እና የቡዛ ) እንዲሁም እናርጅ እናውጋ ወረዳ 3 ቀበሌዎች (የጎሳ፣ታሞ ዳዋሮ እና ጥጣር ባድማ) በድምሩ 36 ሺህ 500 ነዋሪዎችን በስነ-ምግብ እና ስነ-ፅዳት ዙሪያ የባህሪ ለውጥ እና መሻሻል እንዲያመጡ እየሰራ ይገኛል፡፡

 


Language Selection
ሶሻል ሚዲያ
FacebookTwitter
ምርጥ ተሞክሮ
የጎብኝዎች ብዛት
Today23
Week345
All86766

Currently are 16 guests online


ምርጫ
ስለ ድረ-ገፅ ያለዎት አስተያየት ?