አመልድ ኢትዮጵያ 648 ሺህ 540 ተፈናቃዮች ድጋፍ ያደርጋል፡፡የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር / ዓለማየሁ ዋሴ

      emergency assistance

አመልድ ኢትዮጵያ ከሰሜንና ደቡብ ወሎ፤ ዋግኸምራ ዞን እንዲሁም በአጎራባች አፋር ክልል በጦርነቱ ሳቢያ ወገኖች ላይ ከፍተኛ የሆነ የሰብዓዊ እና ቁሳዊ ውድመት ደርሷል፡፡

የክልሉ አደጋ መከላከል፣ ምግብ ዋስትና እና ልዩ ድጋፍ የሚሹ አካባቢዎች ማስተባበሪያ ኮሚሽን መረጃ እንደሚያመላክተው በአማራ ክልል በአጠቃላይ 2 ሚሊዮን 83 ሺህ 278 ወገኖች (ህጻናት፣ ነፍሰ ጡርና አጥቢ ሴቶች፣ አካል ጉዳተኞች፣ አዛውንቶች) ከመኖሪያ ቀያቸው፤ ከሞቀ ጎጆአቸው ተፈናቅለው በተለያዩ ቦታዎች ወድቀዋል፡፡

ከሰሜን ወሎ እና ዋግምራ ዞን እንዲሁም ከአጎራባች ክልል (ከአፋር) ሸሽተው በሐይቅ/ተሁለደሬ፣ ደሴና ኮምቦልቻ ከተሞች ላይ በየት/ቤቱ፣ በግለሰብ ቤትና ሜዳ ላይ ተጠልለው ይገኙ የነበሩ ወገኖቻችን ጦርነቱ እየሰፋ በመሄዱ ለዳግም ስደት የተዳረጉትን ጨምሮ አካባቢያቸውን ለቀው በደ/ብርሃን ከተማና በሰሜን ሽዋ ዞን ሌሎች ወረዳዎች በጊዜያዊ መጠለያ ይገኛሉ፡፡ በዚህ ምክንያት ለከፍተኛ የሆነ የምግብ እንዲሁም ቁሳቁስ እጦት እና መጎሳቆል ተዳርገዋል፡፡

     emergency assistance 1 

ለረሃብ የተጋለጡ ወገኖችን ለመደገፍ የአመልድ ኢትዮጵያ የተቀናጀ አስቸኳይ ጊዜ እርዳታ ፕሮግራም ከሲአርኤስ (CRS) ጋር በመተባበር በጦርነቱ ተፈናቅለው /ብርሃን ከተማ ላይ ለተጠለሉ 318 ሺህ 955 ተፈናቃዮች 47 ሺህ 843 ኩንታል ስንዴ፣ 4 ሺህ 784 ኩንታል አተር ክክ/ጥራጥሬ እና 143 ሺህ 530 ሊትር የምግብ ዘይት እየጓጓዘ ሲሆን በቀጣይ ቀናት ስርጭት እንደሚደረግ የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር / ዓለማየሁ ዋሴ ተናግረዋል፡፡

በመቄት ወረዳ እንዲሁ 265 ሺህ 322 ተፈናቃዮች እና ሃብት ንብረታቸው ወድሞ የሚቀመስ ላጡ ወገኖች ስንዴ 39 ሺህ 798 ኩንታል፣ ጥራጥሬ/የአተር ክክ 3 ሺህ 979 ኩንታል፣ 119 ሺህ 394 ሊትር ዘይት በስርጭት ላይ እንደሚገኝ ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡

ከወልዲያ፣ ጋሸና፣ ጉባላፍቶ፣ አንጎት፣ ጋዞ፣ ቡግና ዋድላ፣ ዝቋላ፣ ጻግብዥ፣ አንጎትና ሌሎች ወረዳዎች በባሕር ዳር ዘንዘልማ ጊዜያዊ መጠለያ ላይ ለሚገኙ 33 ሺህ ተፈናቃዮች 4 ሺህ 950 ኩንታል ስንዴ፣ 495 ኩንታል አተር ክክ እንዲሁም 14 ሺህ 850 ሊትር ዘይት ዝግጁ የተደረገ ሲሆን 11 ሺህ 191 ተፈናቃች በድምሩ 1 ሺህ 897 ኩንታል ስንዴ፣ የአተር ክክ እና የምግብ ዘይት እንዲጠቀሙ ተደርጓል፡፡

      emergency assistance 2

በተጨማሪም በእብናት በለሳ ለሚገኙ 31 ሺህ 263 ተፈናቃዮች በድምሩ 6 ሺህ 564 ኩንታል የምግብ እህል እየተጓጓዘ እንደሚገኝ የድርጅቱ የምግብ እህል አስተዳደርና አስቸኳይ ጊዜ እርዳታ ፕሮግራም ዳይሩክተር አቶ ሙሃመድ ኡስማን አስታውቀዋል፡፡

አመልድ ኢትዮጵያ በድምሩ 648 ሺህ 540 ተፈናቃዮች 97 ሺህ 281 ኩንታል ስንዴ፣ 9 ሺህ 728 ኩንታል አተር ክክ እንዲሁም 291 ሺህ 842 ሊትር የምግብ ዘይት በማሰራጨት ላይ እንደሆነም የፕሮግራም ዳይሬክተሩ ጨምረው አስታውቀዋል፡፡

/ ዓለማየሁ የሰብዓዊ ድጋፍ ለማድረግ ቀናዒ ምላሽ ለሰጡ ለጋሽ ድርጅቶች በተረጂ ወገኖች ስም ምስጋና አቅርበዋል፡፡