ትጉህ አገልጋዮች፤ የጎፍጭማ ታዳጊ ከተማ የውሃ ኮሚቴ

      Diligent Water Committee

መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ለማህበረሰብ ውሃ ተቋማትን ከገነቡ በኋላ ተረክቦ የማስተዳደር ሃላፊነቱ የማህበረሰቡ ነው፡፡ ነገር ግን በአግባቡ ካልተያዙ ማህበረሰቡን ሳያገለግሉ በአጭር ጊዜ ለብልሽት ይዳረጋሉ፡፡ ይህ ችግር በማህበረሰቡ የእኔነት ስሜት እና በጠንካራ የውሃ ኮሚቴዎች የሚፈታ ነው፡፡ ለዚህ አብነት የሚሆነን በአመልድ ኢትዮጵያ የጆንስ ሪግ ዋሽ ፕሮጀክት በደ/ኤልያስ ወረዳ የጎፍጭማ ታዳጊ ከተማ የንፁህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ጠንካራ የውሃ አስተዳደር ኮሚቴ ነው፡፡ የኮሚቴዎች የስራ ጥንካሬ እና ክትትል ማህበረሰቡን የረዥም ጊዜ የንፁህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚነት ያረጋገጥ ሁኗል፡፡

ይህ የጥልቅ ጉድጓድ ንፁህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት 5ሺህ 500 ለሚጠጉ የጎፍጭማ ነዋሪዎች የንፁህ ውሃ አግልግሎት እየሰጠ ይገኛል፡፡ ነዋሪዎች ለዘመናት የንፁህ መጠጥ ውሃ ጥያቄያቸውን የፈታላቸው መሆኑን ይናገራሉ፡፡

       Diligent Water Committee1

የውሃ ተቋሙ 8 አባላት ባሉት የውሃ ኮሚቴ ይተዳደራል፡፡ በውሃ ኮሚቴው በሚደረግለት ንቁ ክትትል እና ጥገና የውሃ ተቋሙ በአግባቡ ጥቅም ላይ እንዲውል አድርጎታል፡፡ አቶ የኔነህ መኮንን የኮሚቴው ሰብሳቢ ናቸው፡፡ ስለጎፍጭማ የውሃ ችግር ሲያስታውሱ ህዝቡ ከተግማ ወንዝ እና ከዘንባል ወራጅ ወንዝ ነበር የሚጠቀመው ይላሉ፡፡ "መንግስት ውሃ ይገባላችኋል ብሎን 14 ዓመት ከጠበቅን በኋላ በአመልድ በኩል ያገኘነው ውሃ ነው፡፡ ስለዚህ የውሃ ተቋሙን ለረዥም ጊዜ እንዲያገለግለን በጥንቃቄ ይዘነዋል፡፡ ለአብነትም 3 ጊዜ የውሃ መስመር ፈንድቶ ጠግነናል፣ በግለሰቦች ቤት ቆጣሪ እየተከልን መስመር እየዘረጋን ተጠቃሚ እንዲሆኑ አድርገናል፤ የውሃ ተጠቃሚዎች ገንዘብ እንዲቆጥቡ በማድረግ ለጥገና የሚያስፈልገውን ገንዝብ በባንክ አስቀምጠናል" ብሏል፡፡

በአጠቀላይ የንፁህ መጠጥ ውሃ ተቋማት ረዥም ጊዜ እንዲያገለግሉ የተጠቃሚው ማህበረሰብ የእኔነት ስሜት እና የውሃ ኮሚቴዎች ቁርጠኝነት ወሳኝ ነው፡፡