የቡችክሲ መስኖ ልማት

       Buchiksi irrigation scheme

አርሶ አደሩ ከዝናብ ጥገኝነት ተላቆ ምርታማ እንዲሆን የመስኖ ልማት ስራዎቻችን ወሳኝ ሚና አላቸው፡፡

አመልድ ኢትዮጵያ የደን ልማት ስራዎችን በማጠናከር፣ ምርታማነትን የሚያሳድጉ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን ለአርሶ አደሩ በማቅረብ፣ የንጹህ መጠጥ ውሃ በማድረስ፣ የግልና የአካባቢ ንጽህናን በመጠበቅና ትራኮማን በመከላከል፣ አነስተኛ የመስኖ አውታሮችን በመዘርጋት፣ ስርዓተ-ምግብን በማሻሻልና መቀንጨርን በመከላከል ከፍተኛ አስተዋጽኦ ሲያደርግ ቆይቷል፡፡

 

አመልድ ኢትዮጵያ 8.4 ሚሊዮን ብር በአዊ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞን በባንጃ ወረዳ የቡችክሲ ዘመናዊ መስኖ አውታር ገንብቷል፡፡ ይህ ዘመናዊ መስኖ 230 ሄክታር መሬት በላይ የሚያለማ ሲሆን 1 ሺህ 360 አባውራና እማዎራ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ አድርጓል፡፡ ከተጠቃሚዎች መካከል የአስኩና አቦ ቀበሌ 7 ልጆች አባት አርሶ አደር ታደለ ፈንታ አንዱ ናቸው፡፡ በመስኖ ያለሙትን ገብስ እያጨዱ ነበር ያገኘናቸው፡፡ የቡችክሲ ዘመናዊ መስኖ አውታር በመገንባቱ በስፋት መስኖ ልማት ላይ እንደገቡ ይናገራሉ፡፡ በፊት በባህላዊ ለማልማት ቢሞክሩም እዚህ ግባ የሚባል እንዳልነበር ገልጸው በአሁኑ ሰዓት ወንዙ በአግባቡ ተጠልፎ በመንደራቸው በመግባቱ ከሁለት ጊዜ በላይ እያለሙ ይገኛሉ፡፡ በፊት ወደ መሬት የሚሰርግና በከንቱ የሚባክን ውሃ፣ ከፍተኛ ጉልበት እና ጊዜ ይጨርሱ ነበር፡፡ በአሁኑ ሰዓት ግን ችግሮች ስለተቀረፉ በመስኖ ሰብሎችን እያለሙ ይገኛሉ፡፡ ከደረሱት ሰብሎቻቸውም በአማካይ ገብስ 10 ኩንታል፣ ድንች 8 ኩንታል፣ ሽንኩርት 8 ኩንታል ምርት እንደሚያገኙ ይጠብቃሉ፡፡