የዋና ዳይሬክተሩ መልዕክት
የአማራ መልሶ መቋቋምና ልማት ድርጅት (አመልድ) በክልላችን ስትራቴጅያዊ ጠቀሜታ ያላቸው የአጭርና የረጅም ጊዜ ፕሮግራሞችንና ፕሮጀክቶችን በመቅረጽ የመንግስትንና የህዝቡን የልማት ክፍተቶች በመሙላት ትርጉም ያለው የልማት ስራ እያከናወነ ይገኛል፡፡
ከዚህ አኳያ አመልድ በዋና ዋና የልማት ምሰሶዎች/ፕሮግራሞች ማለትም በአካባቢና ደን ልማት፣ በንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦትና መስኖ ልማት፣ በግብርናና አደጋ ስጋት ስራ አመራር፣ እንዲሁም የወጣቶች ኢንተርፕራይዝና የግል ሴክተር ልማት ዘርፎች ውጤታማ ስራዎችን በማከናወን ላይ ነው፡፡ በእነዚህ ሰፊ የልማት ፕሮግራሞችና ፕሮጀክቶች ውስጥ ስርዓተ ጾታ፣ የአካል ጉዳተኝነት፣ ባህል፣ ኤችአይቪ/ኤድስ የመከላከል ስራዎችም እንዲካተቱ ተደርጓል፡፡
አመልድ በአሁኑ ሰዓት በአጠቃላይ 1 ሺህ 939 ሰራተኞች አሉት፡፡ ድርጅቱ በ2012/2013 ዓ.ም ከ28 ለጋሾች የተገኘውን 1.42 ቢሊዮን ብር (48 በመቶ የምግብ እህል እርዳታን ጨምሮ) በክልላችን በ47 ወረዳዎች 31 የተቀናጁ ፕሮጀክቶችን (2 አስቸኳይ የምግብ እርዳታ) በመተግበር ከ1.4 ሚሊዮን ህዝብ በላይ ተጠቃሚ አድርጓል፡፡ ድርጅቱ የኮሮና ቫይረስ ከተከሰተበት ጊዜ ጀምሮ ፕሮጀክት በሚተገበርባቸው የክልሉ አካባቢዎች በድምሩ ከ53.9 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ በማድረግ የተለያዩ ቁሳቁሶችን ድጋፍ በማድረግና የሰብዓዊነት ስራ በማከናወን ኃላፊነቱን ተወጥቷል፡፡