የእጅ መታጠብ ቀን በድምቀት ተከበረ

"ለጤናችን ከፍ ይበል እጃችን"

(ጥቅምት 4 ቀን 2008 ዓ.ም ባህር ዳር)

የአማራ መልሶ መቋቋምና ልማት ድርጅት (አመልድ) ሁሉ-አቀፍ የስነ-ጽዳት ፕሮግራም ጽ/ቤት የእጅ መታጠብ ቀንን በአለም አቀፍ ደረጃ ለ8ኛ ጊዜ እንዲሁም በሃገር አቀፍ ደረጃ ለ7ኛ ጊዜ በባህር ዳር ከተማ ሚሌኒየም አደባባይ በድምቀት አክብሯል፡፡

                        hand wash (2)   

የአብክመ ጤና ቢሮ ምክትል ቢሮ ሃላፊ ሲስተር ዘቢደር ኃይሌ በመክፈቻ ንግግራቸው እጅን በውሃና በሳሙና መታጠብ ብቻ በህጻናትም ሆነ አዋቂዎች ላይ ሊያጋጥም የሚችል ስቃይና ሞት ለመከላከል ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው ብለዋል፡፡ ዓለም አቀፍ የእጅ መታጠብ ቀን ከአንደኛ ደረጃ ተማሪዎች ጋር የሚከበረው ህጻናት በተቅማጥና በመተንፈሻ አካል በሽታዎች የበለጠ የሚጋለጡ በመሆናቸው ብቻ ሳይሆን ህጻናት አዲስ አስተሳሰብን ለመቀበልና ለመተግበር ከፍተኛ ተነሳሽነትና ጉጉት ያላቸው በመሆኑ በህብረተሰቡ ዘንድ የባህርይ ለውጥ እንዲመጣ ወሳኝ ሚና መጫወት የሚችሉ በመሆናቸው ነው ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ የጀርመን አግሮ አክሽን ዳይሬክተር ወ/ሮ ትርንጎ ክንፈገብርኤል አመልድ ከለጋሽ ድርጅቶች ጋር በመሆን ሁሉ-አቀፍ የስነ-ጽዳት ፕሮግራም በባህር ዳር ከተማ በሚገኙ 19 ቀበሌዎች 17 የመጸዳጃ ቤቶችን፣ ዘንዘልማና ጢስ ዓባይ የጥልቅ ውሃ ግንባታ፣ በፈለገ-ህይወት ሪፈራል ሆስፒታልና በተለያዩ ት/ቤቶች የማህበረሰብ ሽንት ቤቶችን በመገንባትና በመጠገን ከፍተኛ ርብርብ ማድረጉን ገልጸዋል፡፡

                        hand wash (1)

የአመልድ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር አምላኩ አስረስ በፕሮግራሙ እንደገለጹት አገራችን ኢትዮጵያ የተያያዘችውን መከላከል ላይ ትኩረት ያደረገ የጤና ፖሊሲ ተግባራዊ በማድረግ አብዛኛውን የምዕተ ዓመቱን የልማት ግቦች ማሳካት ችላለች ብለዋል፡፡ በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዘመን የእናቶችንና ህጻናትን ሞት ለመቀነስና በጤና ተቋማት ጥራት ያለው አገልግሎት በመስጠት ይበልጥ ውጤት ለማምጣት ዕቅድ መያዙን ዶ/ር አምላኩ አስታውቀዋል፡፡

የዓለም እጅ መታጠብ ቀን እ.ኤ.አ ከ2008 ጀምሮ በአለም ለ8ኛ ጊዜ፣ በአገራችን ደግሞ ለ7ኛ ጊዜ “ለጤናችን ከፍ ይበል እጃችን" በሚል መሪ-ቃል ከጥቅምት 4-11/2008 ዓ.ም ለአንድ ሳምንት ይከበራል፡፡

እጅ መታጠብ ከንጽህና ጉድለት በሚመጡ ተላላፊ በሽታዎች እንዳይያዙና በህመም ምክንያት የሚጠፋውን ገንዘብ፣ ጊዜ፣ ጉልበትና ምቾት ማጣት በመቀነስ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳው የጎላ በመሆኑ በክልላችን በሚገኙ ት/ቤቶችና ሁሉም አካባቢዎች ተግባራዊ እንዲሆን ለተፈጻሚነቱም የመንግስት አካላት፣መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ የሲቪክ ማህበራት እንዲሁም መላው ህዝብ እንዲረባረብ የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር አምላኩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በፕሮግራሙ ከጤና ጥበቃ ቢሮ፣ ከአመልድ፣ ከጀርመን አግሮ አክሽን፣ ከተለያዩ ት/ቤቶች የተውጣጡ መምህራንና ተማሪዎች ተሳትፈዋል፡፡

Copyright © 2012 ORDA Ethiopia.
All Rights Reserved.