የ2007/2008 ዕቅድ አፈጻጸምና የ2008/2009 ዕቅድ ትውውቅ ተካሄደ

የአማራ መልሶ መቋቋምና ልማት ድርጅት (አመልድ) የ2007/2008 ዕቅድ አፈጻጸምና 2008/2009 በባህር ዳር ከተማ ከመጋቢት 30-ሚያዝያ 2/2008 ዓ.ም አካሂዷል፡፡

ዋና ዳይሬክተሩ ዶ/ር አምላኩ አስረስ የድርጅቱን ዓመታዊ አፈጻጸም ሲያቀርቡ በ2007 ዓ.ም ከ27 ዓለም አቀፍ ለጋሽ ድርጅቶችና ከ4 ቢሮዎች በአጠቃላይ 31 የልማት ድርጅቶች በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ 1.69 ሚሊዮን ህዝብን ተጠቃሚ አድርጓል ብለዋል፡፡

ዋና ዳይሬክተሩ ከሳይንሳዊ የልማት መርህ ጋር አያይዘው እንደገለጹት ድርጅቱ በአሁኑ ሰዓት ጥሩ መሻሻሎች መኖራቸው አውስተው በቀጣይ የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከትና ተግባራትን በማዳከም ልማታዊ አስተሳሰብን ለማጎልበት የሚያስችሉ ተግባራትን ማጠናከር እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

ደርጅቱ በቀጣይ ከ ”NGO” ጥገኝነት ተላቆ የራሱን የገቢ ማስገኛ ተቋማትን ለማደራጀት ከመቼውም ጊዜ በተሻለ ርብርብ እያደረገ እንደሆነም ዶ/ር አምላኩ ገልጸዋል፡፡ በተለይ በዚህ ዓመት የተከሰተዉ ድርቅ በህይወት ላይ የከፋ ጉዳት እንዳያደርስና በእንስሳትና በንብረት ላይ የደረሰዉም ጉዳት እንዲያገግም ለማድረግ በርካታ ስራዎች በመከናወን ላይ ይገኛሉ፡፡ እስካሁን በተደረገዉ ጥረትም ለድርቅ መቋቋሚያ ሥራዎች ማስፈፀሚያ ምግብ አስተዳደር፣ ውሃ መቆፈር፣ የድርቅ መቋቋሚያ ኘሮጀክቶችን ከለጋሽ ድርጅቶች 108 ሚሊዮን ብር በማሰባሰብ የምግብ እህል ከመርዳት ባሻገር 27 ሺህ ኩንታል ዘር ከ9 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች እንዲሰራጭ ተደርጓል፡፡

የድርጅቱ ዋና የትኩረት መስኮች ተለይተው ከመንግስት የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ጋር እንዲጣጣም ተደርጎ የድርጅቱ ስትራቴጅክ ዕቅድ (2016-2020) እንደተዘጋጀም የሃብት ልማት ፕሮግራም ዳይሬክተሩ አቶ ሽመልስ ሙሃመድ አብራርተዋል፡፡ 
በመሆኑም የግብርና ምርታማነትን በማሳደግ፣ ዘላቂነት ያለው የተፈጥሮ ሃብት ስራ በማከናወን፣ የንጹህ መጠጥ ውሃና መስኖ አውታሮችን በመዘርጋት የሴቶችንና ስራ አጥ ወጣቶችን ወደ ስራ ለማስገባት የተያዘውን ዕቅድ ለመፈጸም በቁርጠኝነት መረባረብ እንደሚገባ የድርጅቱ ከፍተኛ ኃላፊዎች አሳስበዋል፡፡

Copyright © 2012 ORDA Ethiopia.
All Rights Reserved.