የእምቦጭ (Water Hyacinth) አረም በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ላይ ጉዳት ሊያስከትል እንደሚችል ተጠቆመ

በታደሰ ዘበአማን 

                                                      Tana13

የእምቦጭ (water hyacinth) ወራሪ አረም በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ላይም ጉዳት ሊያደረስ እንደሚችል ተጠቆመ፡፡ ይህ የተጠቆመው በባህርዳር ከተማ ሆም ላንድ ሆቴል ከታህሳስ 3-4 2007 ዓ.ም. በተካሄደውና ከፌደራል፣ ከክልል፣ ከዞንና ከወረዳ የመጡ አመራሮች የባህርዳር ዩኒቨረሲቲ ምሁራንና ከፍተኛ አመራሮች አንዲሁም ከአመልድ የተወጣጡ አመራሮችና ባለሙያዎች  ባሳተፈው አገር አቀፍ የእንቦጭ አረምን ለመከላል በተዘጋጀው አገር አቀፍ አዉደ ጥናት ላይ ነበር፡፡ አውደ ጥናቱ የተዘጋጀው በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ፣ በአመልድና በአማራ ክልላዊ መንግስት የአካ/ጥ/መ/አስ/አጠ/ቢሮ ትብብር ነው፡፡

የአውደ ጥናቱ አላማ በጣና ሃይቅና በአካባቢው በከፍተኛ ፍጥነት እየተስፋፋ ያለውን  አደገኛ፣ ወራሪና መጤ የሆነውን የእምቦጭ (Water Hyacinth) መከላከል የሚያስችል ስትራቴጅ መንደፍ መሆኑን ዶ/ር ተስፋዬ ሽፈራው የባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዝዳንት  የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ሲያደርጉ ገልፀዋል፡፡

                     Tana12

ክቡር አቶ ከበደ ይማም የአካባቢና ደን ልማት ሚኒስትር ድኤታ በአደረጉት የመግቢያ ንግግር ኢትዮጵያ እያካሄደችው ባለው ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ ላይ የጣና አካባቢ ወሳኝ ነው ብለዋል፡፡ ስለዚህ ይህን አካባቢ ከተጋረጠበት የእምቦጭ አረም ችግር መታደግ ለክልላችን፣ ለሃገራችንና ለአለም ብዙ ትርጉም አለው ብለዋል፡፡ አቶ ከበደ አያይዘውም ይህ አረም በርካታ ጉዳቶች የሚያስከትል ነዉ ከነዚህ ችግሮችም መካከል አገር በቀል እፅዋት እንዲሰደዱ፣ ውሃው እንዲደርቅ፣ የውሃው ኬሚካላዊ ባህሪይንም እንዲለወጥና አሳዎች እንዲሞቱ እንደሚያደርግ ገለፀዋል፡፡

አውደ ጥናቱን በክብር እንግድነት በመገኘት የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተደድር ክቡር አቶ ገዱ አንዳርጋቸውም ይህ ወራሪ አረም እንዲሰፋፋ መፍቀድ በምንም አይነት ሁኔታ ተቀባይነት የለውም ብለዋል፡፡ አቶ ገዱ አያይዘውም አረሙን ለማስወገድ የክልሉ መንግስት ከ2005 ዓ.ም ጀምሮ ከፍተኛ ጥረት እያደረገ እንደሚገኝ ገልፀው አሁንም ቢሆን ይህ ቁርጠኝነት በመንግስታቸው በኩል አንዳለ ገልፀው አጋራ አካላትም በዚህ ዘመቻ ላይ የክልሉን መንግስት እንዲደግፉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

                         Tana11

ይህ አረም በጣና አካባቢ የተከሰተው በ2004 ዓ.ም መሆኑን የገለፁት ደግሞ አቶ ባይህ ጥሩነህ የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት አካ/ጥ/መ/አስ/አጠ/ቢሮ ኃላፊ ናቸው፡፡ አቶ ባህይ ይህን የተናገሩት በእምቦጭ አረም ዙሪያ የአካባቢ ጥበቃና መሬት አስተዳደር ቢሮ ያከናወናቸውን ዋና ዋና ተግባራትና ያጋጠሙትን ተግዳሮቶች የሚገልጽ ፅሁፍ ለተሳታፊዎች ባቀረቡበት ወቅት ነዉ፡፡ ከ2005 አ.ም ጀምሮ በደንቢያ፣ በጎንደር ዙሪያና በሊቦ ከምከም 15 ቀበሌዎች የተስፋፋውን አረም ለማስወገድ ጥረት ተደርጎ ከተወሰነ የደንቢያ ወረዳ አቸራ ቀበሌ ቦታ ላይ ከሚገኝ ውጭ አረሙ ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ የማስወገድ ስራ እንደተሰራ ገልፀዋል፡፡ ነገር ግን አረሙ በሁሉም የአካሉ ክፍሎችና በዘር ስለሚራባ፣ በ6 ና 7 ቀናት ውስጥ በብዙ ቁጥር ስለሚባዛና ከአንድ ዛፍ እስከ 20 ሺህ ዘር ስለሚዘጋጅ በ2006 ከላይ በተገለፁት ቀበሌዎች እንደገና ስለታየ በድጋሜ በዘመቻ ለማስወገድ ተችሏል፡፡  ነገር ግን በ2007 አረሙ የጥቃት አድማሱን በማስፋት ከላይ ከተጠቀሱት ወረዳዎች በተጨማሪ በፎገራና በደራ ወረዳዎችም ሊከሰት ችሏል፡፡ ስለሆነም በአሁኑ ጊዜ በአምስት ወረዳዎች በ19 ቀበሌዎች ከ40000 ሄክታር በላይ ቦታ ተንሰራፍቶ የሚገኘውን አረም ለማስወገድ ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡

ነገር ግን አረሙ በፍጥነት የሚሰፋፋ መሆኑ፣ ለተከታታይ ቀናት ብቻ ሳይሆን ለሳምንታት ውሃ ውስጥ ተነክሮ አረሙን የማስወገድ ስራ አሰልችነት ባህሪ መኖሩ፣ ጥልቀት ባለው የውሃ አካል አረሙን ገብቶ ማስወገድ አለመቻል፣ ከጀልባ ላይ ሆኖ ማስወገድም ብዙ ውጤታማ አለመሆንና የተቀናጀ የልማትና የእንክብካቤ ስራ ለመስራት የሚያስችል ፕሮጀክት ቢቀረጽም የገንዘብ እጥረት ስለገጠመ ወደ ስራ ማስገባት አለመቻል በአረም ማስወገድ ስራው ላይ ያጋጠሙ አበይት ችግሮች መሆናቸውን አቶ ባይህ አብራርተዋል፡፡

በአውደ ጥናቱ ላይ ሌላው ጽሁፍ ያቀረቡትና የባህርዳር ዩኒቨርሲቲ መምህር የሆኑት ዶ/ር ዋሴ አንተነህ ናቸው፡፡ ዶ/ር ዋሴ ያቀረቡት ፅሁፍ የእምቦጭ አረም ስርጭት በጣና ሃይቅ ላይ ምን ይመስላል የሚል ርዕስ ነበረው፡፡ ዶ/ር ዋሴም በጽሁፋቸው እንዳብራሩት የእምቦጭ አረም ወደ ጣና ሃይቅ ሊገባ የቻለበት መንገድ በእርግጠኛነት ይህ ነው ብሎ መናገር ባይቻልም ነገር ግን የተለያዩ መላምቶችን ማስቀመጥ እንደሚቻል አብራርተዋል፡፡ ከነዚህም ውስጥ ምን አልባት በአበባው አካባቢን ለማስዋብ፣ ለውሃ ማጥሪያነት፣ ከአሳ ማስገሪያ መረብ ጋር ወይንም ከጀልባዎች ጋር ተጣብቆ መጥቶ ሊሆን እንደሚችል ግምት እንዳለ ገልፀዋል፡፡  አረሙ በአሁኑ ወቅት በአስደንጋጭ ፍጥነት እየተሰራጨ ስለሆነ በዚህ ፍጥነት ከቀጠለ ከጣና ሃይቅ አልፎ ወደ አባይ ወንዝ በመግባት በተራዘመ ሂደት ደግሞ ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብም አደጋ የማይሆንበት ምክንያት እንደሌለ ገልፀዋል፡፡ ይህም ማለት የእምቦጭ አረም ችግር በአሁኑ ጊዜ በአረሙ እየተጠቁ ያሉ ቀበሌዎችና ወረዳዎች ብሎም የዚህ ክልል ችግር ብቻ ሳይሆን የሃገሪቱም  ብሎም የአለም አቀፍም ችግር ስለሆነ ሁሉም ሰው ችግሩን ለማስወገድ ርብርብ ማድረግ እንዳለበት ተናግረዋል፡፡

                                                  Tana14

                                        የአውደ ጥናቱ ተሳታፊዎች በመስክ ጉብኝት ላይ

በሁለተኛው ቀንም ማለትም ቅዳሜ ታህሳስ 4/2007 ዓ.ም ደግሞ የአውደ ጥናቱ ተሳታፊዎች በሰሜን ጎንደር ዞን በጎንደር ዙሪያ ወረዳ ውስጥ በሚገኘዉ በአረሙ በተወረረው ቀበሌ በመገኘት የአረሙን የጥቃት መጠን በአይናቸው ለማየት ችለዋል፡፡ ብዙዎቹ የጉብኝቱ ተሳታፊዎችም የአረሙ መጠን በጣም አስደንጋጭ ነው ሲሉ ተደምጠዋል፡፡

                                                    Tana15

                                      የጎንደር ዙሪያ አርሶ አደሮች የመጤ አረሙን የማስወገድ እልህ አስጨራሽ ስራ በመስራት ላይ

አረሙን ለመከላከል የሚያስችል ስትራቴጅክ ዕቀድም ለአውደ ጥናቱ ተሳተፊዎች ቀርቦ ሰፊ የማዳበሪያ ውይይት ተደርጎበት በአስቸኳይ ወደ ስራ እንዲገባ ተወስኗል፡፡

በመጨረሻም ለአውደ ጥናቱ መሳካት ከፍተኛ ሚና ለተጫወቱ ግለሰቦች የእውቅናና የምስጋና የምስክር ወረቀት በክብር እንግዳው እጅ በክቡር አቶ ከበደ ይማም የአካባቢና የደን ልማት ሚኒሰትር ዲኤታ ተሰጥቶ አውደ ጥናቱ ተጠናቋል፡፡

Copyright © 2012 ORDA Ethiopia.
All Rights Reserved.