የአመልድ ሚሊያር ፕሮጀክት የብዙ ሰዎችን ኑሮ መቀየር መቻሉና ከድርቅ አደጋ መታደጉ ተገለፀ

በታደሰ ዘበአማን

  • የሚሊያር ፕሮጀክት አስትባባሪ ኮሚቴ 4ኛውን አመታዊ ስብሰባውን አካሄደ፡፡
  • 60%  በላይ የሆኑት የሚሊያር ፕሮጀክት ተጠቃሚዎች ከምግብ ዋስትና ፕሮግራም እንደሚመረቁ ተጠቆመ፡፡
                          milear (4)

በአማራ መልሶ መቋቋምና ልማት ድርጅት (አመልድ) ፈፃሚነት፣ በካናዳ መንግስት አለም አቀፍ ጉዳዮችና በካናዳዊያን ልጆችን እንመግብ ድርጅት የገንዘብና የቴክኒክ ድጋፍ  በአማራ ክልል የኦሮሞ ብሔረሰብ ዞን አርጡማ ፉርሲና ደዋ ጨፋ ወረዳዎች እየተፈፀመ የሚገኘው የገበያ መር የኑሮ ማሻሻያ በምስራቅ አማራ (ሚሊያር) ፕሮጀክት የተጠቃሚዎችን ኑሮ በአጅጉ እየለወጠ ያለና ሌሎችም ብዙ ሊማሩበት የሚገባ እንደሆነ የአመልድ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር አምላኩ አስረስ ተናገሩ፡፡ ዳይሬክተሩ ይህን የተናገሩት በኬሚሴ ከተማ ጨፋ ሚሌ ሆቴል ውስጥ ከመጋቢት 7-8፣ 2008 ዓ.ም በተካሄደው 4ኛው የሚሊያር ፕሮጀክት ስቲሪንግ ኮሚቴ ስበሰባ ላይ ተገኝተው የመከፈቻ ንግግር ሲያደርጉ ነው፡፡ ዶክተር አምላኩ አያይዘውም ለዚህ አባባላቸው ምክንያቱን ሲገልፁ አብዛኛው የሃገሪቱ ክፍል በድርቅ አደጋ ተመትቶ ባለበት ወቅት የሚሊያር ፕሮጀክት ተጠቃሚዎች ግን የድርቅ ሰለባ ሳይሆኑ የቀሩበት ሁኔታ ነው ያለው ብለዋል፡፡

ዶ/ር አምላኩ አያይዘውም 40 ሺህ ከሚሆኑት የፕሮጀክቱ ተጠቃሚዎች መካከል 60 በመቶ የሚሆኑት ከምግብ ዋስትና ፕሮግራም እንደሚመረቁ ገልፀዋል፡፡ ዶ/ር አምላኩ ለዚህ ውጤት መምጣት አስተዋፅኦ ላደረጉ የፕሮጀክት ሰራተኞች፣ ለመንግስትና ለረጅ ድርጅቶች እንኳን ደስ ያላችሁ ብለዋል፡፡ 

milear (1)

ሙሃመድ አረጋዊ ይባላል በደዋ ጨፋ ቀበሌ የተረፍ ቀበሌ ነዋሪ ነው፡፡የፕሮጀከቱ ተጠቃሚ ነው፡፡ የስብሰባው ተሳታፊዎች ከጎበኙት አርሶ አደር መካከል አንዱ ነው፡፡ ስለራሱ ህይወትና በፕሮጀክቱ ስላገኘው ጥቅም እንዲህ ያብራራል፡፡ አንዴ የአባቱን በሬ አሽጦ  ሌላ ጊዜ ደግሞ እህቱን አስከፍሎ ሶስት ጊዜ ወደ ሳኡዲ አረቢያ ሄዶ የነበር ሲሆን ሶስቱንም ጊዜ ግን በሳኡዲ መንግስት ተጠርንፎ  ተመልሷል፡፡ አራተኛ ጊዜ ወደ ሳኡዲ ከምሄድ ግን ጉድጓድ ቆፍሬ ውሃ አውጥቼ በመስኖ ማልማት አለብኝ በማለት በማሰብ  የዛሬ ሁለት ዓመታት ጀምሮ ጉድጓድ ወደ መቆፈር ነበር የገባው፡፡ ነገር ግን ጉድጓዱ እየተናደበት ተቸግሮ ነበር፡፡ ይህኔ የአመልድ ሚሊያር ፕሮጀክት  ጉድጓዱ እንዳይናድበት በኮንክሪት ግንብ ገንብቶለታል፡፡ በአመት ሶስት ጊዜ ማምረት ችሏል፡፡ አምና ካመረተው ምርት ሸጦ 112,000.-ብር ገቢ አግኝቷል፡፡ዘንድሮ ግን በዋጋ መቀነስና በምርት ማነስ ምክንያት ገቢው ቀንሷል፡፡ ቢሆንም ግን ዘንድሮም ቢሆን ህዳር ላይ አንድ ጊዜ ምርት ሰብስቦ ሲያበቃ አሁን ሁለተኛ ጊዜ ዘርቶ ነው የሚገኘው፡፡ በዚህ አመት 26000 ብር ገቢ አግኝቷል፡፡ አሁን ደግሞ ማሾ ዘርቷል፡፡ማሳው ላይም ከሽንኩረት በተጨማሪ  18 ማንጎና 76 ዕግር ሙዝ ቋሚ ተክሎችን ተክሏል፡፡የገበያ ችግር ከተፈታለት ወደፊት ብዙ ጥቅም እንደሚያገኝም ያምናል፡፡

 የፕሮጀክቱ አስትባባሪ ኮሚቴ አባላት የተወከሉት ከክልል እስከ ወረዳ የሚገኙ የሚመለከታቸው የመንግስት አካላት፣ ከካናዳ መንግስት የአለም አቀፍ ጉዳዮች ፣ከከናዳዊያን ልጆችን እንመግብ ድርጅትና ከአመልድ ነው፡፡ ኮሚቴው በየአመቱ እየተገናኘ ለፕሮጀክቱ አፈፃፀም መቃናት የሚረዱ አቅጣጫዎችን ያስቀምጣል የፕሮጀክቱን አመታዊ ዕቅድና ሪፖርትም ይገመግማል፡፡ ይህ የአሁኑ ስብሰባ 4ኛው ስብሰባ ሲሆን እስካሁን ከተደረጉት ስብሰባዎችም ይበልጥ ፍሬያማ እንደሆነ ተሳታፊዎች ገልፀዋል፡፡

የአስተባባሪ ኮሚቴው ስብሰባ ላይ የ2015 የፕሮጀክቱ አፈፃፀም ሪፖርት፣ የ2015 አመታዊ የግምገማ ጥናት ሪፖርትና የ2016-17 አመታዊ የስራ እቅድ ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸውል፡፡ ከአዳራሽ ውይይት በተጨማሪም በፕሮጀክቱ 3 ቀበሌዎች የሚገኙ የተለያዩ ስራዎች በተሰብሳቢዎች ተጎብኝተዋል፡፡ 

የስብሰባው ተሳታፊ ከነበሩት መካከል አንዱ ዶ/ር ተሾመ ዋለ የክልሉ የግበርና ቢሮ ኃላፊ የሚሊያር ፕሮጀክት በምስራቅ አማራ ካሉ ፕሮጀክቶች መካከል አመርቂ ውጤት ያለው እንደሆነ ገልፀዋል፡፡  ዶ/ር ተሾመ አያይዘውም ፕሮጀክቱ 24 በመቶ የሚሆኑት ተጠቃሚዎቹ ሴት እማወራዎች መሆናቸው፣ በየአመቱ ደግሞ የለውጥ ግምገማ ጥናት የሚያደርግ መሆኑና ቆጣቢ የሆነ የሃብት አጠቃቀም ያለው መሆኑ ለየት የሚያደርጉት ባህሪያቶቹ ናቸው ብለዋል፡፡ ዶ/ር ተሾመ ዋለ አያይዘውም የፕሮጀክቱ ምርጥ አፈፃፀም ወደ ሌሎች አካባቢዎች ማስፋት በሚቻልበት መንገድ ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ መቀመር አለበት ብለዋል፡፡ 

milear (2)

አሚናት ተሰማ ትባላለች በደዋ ጨፋ ወረዳ የጉር ቀበሌ ነዋሪ ነች፡፡ አሷም በበኩሏ ለጎብኝዎቸ እንዲህ ብላለች፡፡

አመልድ ከመጣ ጀምሮ ብዙ ጥቅም አግኝተናል፡፡ ለምሳሌ የአትክልት ዘር ብር 900 ነበር አመልድ ከመጣ ወዲህ ግን ብር 400 አይቀረብልን ነው፡፡ ከ2006 ወደዚህ ህይወታችን ተቀይሯል፡፡ ከባሌ ጋር ከሌሊቱ 10፡00 ሠዓት ተነስተን ወደ እርሻ እንሄደለን፡፡ አሱ ሲያርስ እኔ እጎለጉላለሁ፡፡ ቤት ስንሄድ እኔ እንጀራ ስጋግር አሱ ውሃ ይቀዳል፡፡ ድሮ ትንሽ የሳር ቤት ነው የነበረን አሁን ግን ባለ 70 ቆርቆሮ ቤት ሰርተናል፡፡ 7 ከብቶች አሉኝ፡፡ ልጆቻችንን እያስተማርን ነው፡፡ አምና ጥሩ አምርተን እስከ 60000 ብር ገቢ አግኝተናል፡፡ ዘንድሮ ግን የሽንኩረት ዋጋ በጣም ስለወረደ ብዙም አልተጠቀምንም፡፡ ቢሆንም ግን በዚህ አመት እስካሁን 40 ኩ/ል ሽንኩርት አንዱን በሁለት መቶ ብር ሂሳብ በመሸጥ ብር 8000.- ብር አግኝተናል፡፡ በቀጣይመ ጠንክረን እንሰራለን ብላለች፡፡

ሚሊያር ፕሮጀክት የአምስት አመት ፕሮጀክት ነው፡፡ ፕሮጀክቱ እስካሁን አራት አመታት ተግባራዊ የተደረገ ሲሆን አምስተኛ አመቱን እየጀመረ ይገኛል፡፡ ፕሮጀክቱ በ10 የአርጡማ ፉርሲና በ4 የደዋ ጨፋ ወረዳዎች ውስጥ ነው እየተተገበረ ያለው፡፡ የሚሊያር ፕሮጀክት ግብ በሁለቱ በአርጡማ ፉርሲና በዳዋ ጨፋ 14 ቀበሌዎች የሚኖሩ 40000 የሚሆኑ ወንዶች፣ ሴቶች፣ ወጣቶችና ህፃናት በገበያ መር ልማት ስራዎች ኑሯቸው እንዲሻሻል ማድረግ ነው፡፡ የመስኖ ልማት ማስፋፋት፣ የአካባቢ እንክብካቤ፣ የእንስሳት ሃብትንና ከእርሻ ውጭ ተግባራትን ማስፋፋት፣ የገበያ ልማት፣ የፕሮጀክት ፈፃሚ አካላትን አቅም ማጎልበትና ስርአተ-ፆታን አካቶ መፈፀም የሚሉት ዋነኛ የፕሮጀክቱ ተግባራት ናቸው፡፡  

milear (3)

ኢብራሂም አሊ ይባላል በደዋ ጨፋ ወረዳ የተረፍ ቀበሌ ነዋሪ ነው፡፡ ስለ ስራውና ስለ በአካባቢያቸው የአመልድ ሚሊያር ፕሮጀክት ያስገኘላቸውን ጥቅም እንዲህ በጉብኝት ላይ ቡድን እንዲህ ያብራራል፡፡

“በአካባቢያችን አመልድ ከመምጣቱ በፊት ማሳቸን በአገዳ እህል ነበር የሚሸፈነው፡፡  የምናገኘውም ምርት በጣም አነስተኛ ነበር፡፡ ማሳቸን ላይ ድሮ ቢሆን በአሁኑ ሰዓት እንስሳት ቆሞበት ነበር የሚታየው፡፡ በዝናብ ወቅት አካባቢው በጎርፍ ነበር የሚጥለቀለቀው፡፡ በዚህም ምክንያት መንግስትን እርዳታ እንጠይቅ ነበር፡፡ እዚህ ላይ እንዲህ ዓይነት ውሃ ይፈልቃል የሚል ነገር ስላልነበረን ከብቶቻችንን ቦርከና ሄደን ነበር የምናጠጣ፡፡ መንግስትና አመልድ ይህን አይተው ከርሰ ምድር ውሃ አውጥታችሁ መጠቀም አለባችሁ ብለው አስተማሩን፡፡የዞን አስተዳዳሪውና ምክትል አስተዳዳሪው ሳይቀሩ እኛ ጋር እየዋሉ እያደሩ አስተምረውናል፡፡ መጀመሪያ አላመንናቸውም ነበር፡፡ ኃላ ላይ ግን ውሃ ወጥቶ ስናየው ተለውጠናል፡፡ ይህ የምታዩት ማሳ ድሮ ቢሆን እንዲህ አረንጓዴ ለብሶ አታዩትም ከብቶች ቆመውበት ነበር የምታገኙት፡፡ አሁን ግን አንድ ወይም ሁለት ኩሬ የሌለው አርሶ አደር የለም፡፡ የከርሰ ምድር ውሃ መጠቀም የጀመርነው ከባለፉት ሶስት አመታት ጅምሮ ነው፡፡ ጉድጓድ ለመቆፈር ከ10-15 ቀናት ይፈጅብናል፡፡ በዓመት ሶስት ጊዜ ማምረት ጀምረናል በዚያም ምክንያት ገቢያችን ጨምሯል፡፡ ዘንድሮ ግን የምርት መሸጫ ዋጋ ስለቀነሰ ችግር አጋጥሞናል፡፡ ባለፉት ሁለት አመታት ጥሩ ገቢ ነበር ያገኘን ነገር ግ ን በዚህ ዓመት ገቢያችን በዋጋ መቀነስ ምክንያት በጣም ቀንሷል፡፡

ከአሁን በፊት ባለን መሬት ላይ ከ4-5 ኩ/ል ምርት ብቻ ነበር የምናገኘው፡፡ አሁን ግን በአመት ሶስት ጊዜ ማምረት ችያለሁ፡፡ በዚህም ምክንያት ሃብት ማፍራት ጀምሬያለሁ፡፡ ለምሳሌ ባለ 120 ቆርቆሮ ቤት ሰርቻለሁ፡፡ በ187000 ብር ከተማ ቤት ገዝቻለሁ፡፡ እሱንም እያከራየሁ በየወሩ ገቢ እያገኘሁ ነው፡፡ በባንክም ብር ቆጥቤያለሁ፡፡ ካለኝ ሶስት ጥማድ መሬት በተጨማሪ እየተከራየሁ ማረስ ጀምሬያለሁ፡፡ ሻይ ቤትም ከፍቻለሁ፡፡”

 የፕሮጀክቱ ሪፖርት እንደሚጠቁመው ፈጥኖ የሚደርሱ ምርጥ የእህል ዘርና የተሻሻለ የግብርና ዘዴ የተጠቀሙ የፕሮጀክቱ ተጠቃሚ አርሶ አደሮች በዚህ ድርቅ ወቅት ማሽላና ጤፍ በሄ/ር በአማካይ 11.36 ኩ/ልና 7.47 ኩ/ል ምርት ያገኙ ሲሆን ሌሎች አ/አደሮች ግን ምንም ምርት ሳያገኙ የቀረበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ በፕሮጀክቱ ላይ በተደረገ አመታዊ የፕሮጀክት ለውጥ ግምገማ ጥናት የመስኖ ተጠቃሚ ሰዎች ቁጥር ከፕሮጀክቱ መጀመሪያ ላይ ከነበረው 16% የመነሻ መጠን በ2015 መጨረሻ ላ ወደ 53 በመቶ አድጓል፡፡ የሽንኩርት ምርታማነት ደግሞ ከ51 ኩንታል በሄ/ር ከነበረበት ወደ 290 ኩ/ል በሄ/ር፤ የቲማቲም ደግሞ ከ26 ኩ/ል በሄ/ር ወደ 101 ኩ/ል በሄ/ር ያደገበት ሁኔታ እንዳለ አመታዊ ጥናቱ አመላክቷል፡፡

በኢትዮጵያ የካናዳ ኤምባሲ ውስጥ የካናዳ አለም አቀፍ ጉዳዮች የምግብ ዋስትና አና የግብርና እድገት ቡድን መሪ የሆኑት ወ/ሮ አበበች አሰፋ  በበኩላቸው በፕሮጀክቱ የስርዓተ-ፆታ፣ በመስኖ እንቅስቃሴ ና በፕሮጀክት፣ በመንግስትና በማህበረሰቡ መካከል ያለው ቅንጅትውጤማነት በጣም እንደተደነቁ ገልፀው ይህን መልካም አፈፃፀም በመቀመር ወደሌለች አካባቢዎች ማስፋት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ ወ/ሮ አበበች አያይዘውም ሴቶች በእርሻ ስራ ላይ የበለጠ ተሳትፎ እንዲኖራቸው ማድረግ አለብን እንዲሁም የተከሰተውን የምርት ገበያ ችግርን ለመቅረፍ ሁላችንም መረባረብ አለብን ብለዋል፡፡

የካናዳውያን ህጻናትን እንመግብ ድርጅት ዋና ስራ አስፈፃሚና ፕሬዝዳንት የሆኑት ወ/ሮ ዴብራ ከርቢ በበኩላቸው በመስክ ያዩት የስርዓተ-ፆታ ስራ ተቀምሮ ወደ ሌሎች ድርጅታቸው ወደሚሰራባቸው ሃገራት ሊሰፋ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

                      milear (5)milear (6)

የስቲሪንግ ኮሚቴ አባላት የመስክ ጉብኝት አድርገዋል፡፡ በመጀመሪያም የሄዱት በዳዋ ጨፋ ወረዳ ውስጥ ወደ ሚገኘው ተረፍ ቀበሌ ነበር፡፡ በዚህም ቀበሌ ነዋሪ ከሆኑና የፕሮጀክቱ ተጠቃሚ ከሆኑ ግለሰቦች ጋር ተወይተዋል፡፡ ከዛም በመቀጠል ለቦርከና ማህበራት ዩኒዮን አገልግሎት የሚውል በፕሮጀክቱ የተገነባ መጋዝን ነው የተጎበኘው፡፡ በቀጣዩ ቀን ደግሞ በአርጡማ ፉርሲ ወረዳ ወደሚገኙ አሸዋ ሉጢና ኤዱ መድኔ ቀበሌ የሚገኙ የመስኖ ልማት፣ የሰርአተ-ፆታና የመንደር ቁጠባና ብድር ቡድኖችን ተመልክተዋል፡፡ በጉብኝቱ ተሳታፊ ከነበሩት መካከል አንዷ የሆኑት የተከበሩ ወ/ሮ ፋንታዬ ጥበቡ የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት የሴቶችና ህፃናት ጉዳዮች ቢሮ ሃላፊ በበኩላቸው በአዩት ነገር በጣም የተደሰቱ መሆኑን ገልፀው ከዛ ውጭ ግን ይህ ጉብኝት ለእርሳቸው ትልቅ የቤተ ሥራ እንዲወስዱ እንዳነሳሳቸው አክለዋል፡፡ ስለዚህም ወደፊት ከአመልድ ጋር በመተባበር በፕሮጀክቱ የተገኘውን በጣም ውጤታማ የሆነ የስርዓተ-ፆታ ስራዎች ወደ ሌሎች ቦታዎች እንዴት እንደምናሰፋው እንነጋገራለን በማለት አክለዋል የተከበሩ ወ/ሮ ፋንታዮ ጥበቡ፡፡

በመጨረሻም ተሰብሳቢዎች በፕሮጀክቱ እ.ኤ.አ የ2016-17 ዓ.ም እቅድና በአጠቃላይ ጉዳዮች ላይ ከተወያዩ በኃላ ስብሰባው ተጠናቋል፡፡

Copyright © 2012 ORDA Ethiopia.
All Rights Reserved.