Joomla TemplatesBest Web HostingBest Joomla Hosting

ዋና ገፅ ዜና የቅርብ ዜናዎች ድህነትን የዘረረው ባለ መስኖው ቡጢኛ አርሶ አደር

                    ድህነትን የዘረረው ባለ መስኖው ቡጢኛ አርሶ አደር

          safe-water


የአማራ መልሶ መቋቋምና ልማት ድርጅት (አመልድ) ስትራቴጅያዊ ጠቀሜታ ያላቸው አጭርና የረጅም ጊዜ ፕሮግራሞችንና ፕሮጀክቶችን በመቅረጽ የመንግስትንና የህዝቡን የልማት ክፍተቶች በመሙላት ትርጉም ያለው የልማት ስራ እያከናወነ ይገኛል፡፡ አመልድ የጉና ተራራ አዋሳኝ ወረዳዎች ላይ የተከሰተውን የብዝሃ-ህይወት መመናመን፣ የአፈር ክለት፣ ልቅ ግጦሽ፣ የመሬት መራቆት፣ የምርታማነት መቀነስ እንዲሁም አማራጭ የኑሮ ማሻሻያ ውስንነቶችን ለመቅረፍ የሚያስችሉ ቴክኖሎጅዎችንና አሰራሮችን በመተግበር ዓላማውን ለማሳካት ብርቱ ጥረት ላይ ነው፡፡

 

ድርጅቱ ከአለም አቀፍ የግብርና ልማት ፈንድ እና ከክልሉ መንግስት በተገኘ 37.3 ሚሊዮን ብር የገንዘብ ድጋፍ 3 ዓመታት የጣና ሃይቅ ተፋሰስ ልማትን መሰረት ያደረገ ማኅበረሰብ አቀፍ የተቀናጀ የተፈጥሮ ሃብት አያያዝ (ኢፋድ ጉና) ፕሮጀክት በደቡብ ጎንደር ዞን ማለትም ፋርጣ፣ ላይ ጋይንትና እስቴ ወረዳዎች በተመረጡ 15 ቀበሌዎች ተግባራዊ እያደረገ ይገኛል፡፡ ይህ ፕሮጀክት 51, 184 ሄክታር መሬት የሚሸፍን ሲሆን 15 ቀበሌዎች ከሚገኙት 23 ሺህ አባውራና እማውራዎች ውስጥ 8 ሺህ የቤተሰብ ሃላፊዎችን (40 ሺህ ሰዎችን) በቀጥታ ተጠቃሚ ያደርጋል፡፡

 

ፕሮጀክቱ በአጣ መኸርና አርጋ መኸር ቀበሌዎች ለሚኖሩ 1, 232 የቤተሰብ ሃላፊዎች (91 እማዎራዎች) ኑሮን የሚያሻሽሉ 17 አነስተኛ የመስኖ ቴክኖሎጅ /የሮፕና ዋሸር ፓምፕ/ 13, 298 የጌሾ ችግኝ፣ 107 ኩንታል ከበሽታ የጸዳ የድንች ኮረት፣ 2,901 የተዳቀለ የአፕል ችግኝ፣ 4 ኪሎ ግራም የአትክልት ዘር/ካሮት፣ ቆስጣ፣ ጥቅል ጎመን፣ ሰላጣ/ 162 ኩንታል የእንስሳት መኖ፣ 166 የማገዶ ቆጣቢ ምድጃ፣ 9 ባዮጋዝ፣ 42 ሜትር ኪዩብ ኮምፖስት ዝግጅት፣ 396 በጸሃይ ብርሃን የሚሰራ የሃይል አቅርቦት እንዲሰራጭ አድርጓል፡፡

 

ከፕሮጀክቱ ግቦች መካከል ደግሞ የተለያዩ የጎርፍ መቀልበሻዎችን በመስራት የእርጥበት ዕቀባን ለመጨመር፣ የትምህርና ማኅበራዊ አገልግሎቶችን ማጠናከርና የደንና ጥምር ደን፣ አማራጭ የሃይል አቅርቦት፣ የውሃ ሃብት ልማት፣ የአፈርን ለምነት እንዲሁም የግብርና ምርታማነትን የሚሳድጉ ቴክኖሎጅዎችን ለአርሶ አደሩ በማቅረብ ኑሯቸው እንዲለወጡ ማስቻል ነው፡፡

              safe-water1
አመልድ አርሶ አደሮችን በተፋሰስ ልማት እንዲሳተፉ በማድረግ ለውጥ ማየት ጀምሯል፡፡ መልካም ለውጥ ካሳዩት መካከል አርሶ አደር ክንዳለም ፈለቀ አንዱ ነው፡፡ በጉና በጌምድር (የቀድሞው ፋርጣ) ወረዳ አርጋ ድድም ቀበሌ እንሰት ጎጥ ኗሪ ነው፡፡ አርሶ አደሩ ከባለቤቱ ከወ/ አለምናት ፈንታ ጋር ሁለት ወንድ እና ሁለት ሴት ልጆችን አፍርተው በማስተማር ላይ ይገኛሉ። አርሶ አደሩ ሩብ ሄክታር ብቻ የእርሻ መሬት ያለው በመሆኑ ማሳውን ከድንች፣ ስንዴና ትሪቲካሌ (ሎጋው ሽቦ) ውጭ ሌላ ሰብል ማምረት አይችልም ነበር፡፡ በተጨማሪ ከዚህ አነስተኛ ማሳ የሚያገኘው ምርት እዚህ ግባ የማይባል የቤተሰቡን ዓመታዊ ቀለብ የማይሸፍን ስለነበረ በመንግስት የምግብ እርዳታ ፕሮግራም ሲደገፍ ኖሯል፡፡ ከዚህ ባሻገር አርሶ አደር ክንዳለም በድህነት የተጎሳቆለውን ጎጆ ለማቃናት ሲል የቤት ወጭዎችን (እንደ ስኳር፣ የምግብ ዘይት፣ ጨው፣ ሽንኩርት፣ ሳሞና) እና የግብርና ግብዓቶችን ለማሟላት በተደጋጋሚ ብድር ይወስድ ነበር፡፡


አርሶ አደሩ ድህነትን ለማሸነፍ ካለው ጉጉት የተነሳ 6 ሺህ ብር ተበድሮ በግ ለማርባት ቢሞክርም ከእንቅርት ላይ ጀሮ ደግፍ እንዲሉ በመሞታቸው ምክንያት ኪሳራ ላይ ጣለው፡፡ ለግብርና ግብዓት ጨምሮ ያመጣውን ብድር በጊዜው ባለመመለሱ ከወለዱ ጋር 12 ሺህ ብር በመድረሱ ኑሮውን ይበልጥ ዳገት አድርጎበት ነበር፡፡ ከችግሩ ብሶ እዳውን መክፈል ባለመቻሉ በአካባቢው ማኅበረሰብ ዘንድ ክብር አሳጥቶት ነበር፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘም ቀየውን ጥሎ ሊሰደድ እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትውስታው ነው፡፡

በዚህ መካከል የአመልድ ኢፋድ ጉና ፕሮጀት ደረሰለት፡፡ ማሳውን አቋርጣ የምታልፈውን የእንሰት ምንጭ ተጠቅሞ እንዲያለማ አስፈላጊው የግብርና ግብዓት በፕሮጀክቱ ቀረበለት፡፡ አካፋ፣ መኮትኮቻ፣ የአትክልት ውሃ ማጠጫ (ማርከፍከፊያ) የፍራፍሬና አትክልት ዘር ቀርቦለት 2004 . ጀምሮ በመስኖ ማልማት ጀመረ፡፡

በመሆኑም ባለ ሙሉ ተስፋው ክንዳለም ለመለወጥ ባደረገው ጥረት 2004 . በዓመት 3 ጊዜ አትክልትና ፍራፍሬ አልምቶ በመሸጥ የነበረበትን 12 ሺህ ብር ዕዳ ከመመለሱ ባሻገር ለቤተሰቡ የዓመት ቀለብ የሚሆን 5 ኩንታል ጤፍ አሟላ። በዚህ የተነሳሳው አርሶ አደር 2005 እና 2006 . ሌት ተቀን በመስራቱ የቤተሰብ ቀለብ አሟልቶ ከሳር ክዳን ወደ ባለ 53 ዚንጎ ቆርቆሮ መኖሪያ ቤት እንዲሁም ሰንጋ ከነኮረቻው 10 ሺህ ብር መግዛት ችሏል፡፡

2007 2008 እና 2009 ተከታታይ ዓመታት እንዲሁ የጓሮ ልማቱን በማስፋት እየሰራ ሲሆን ጥቅል ጎመን፣ ቆስጣ፣ ሰላጣ፣ ካሮትና የአፕል ምርት በመሸጥ ለቀለብ እህል፣ ለቤተሰቡ ቅያር ልብስ፣ ለልጆቹ የትምህርት ቁሳቁስ፣ ለቤት አስቤዛ (ሽንኩርት፣ ዘይት) ያለምንም ችግር ማሟላት ችሏል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ባተሌው አርሶ አደሩ ሃብት ማፍራት፤ ጥሪት መቋጠር ጀምሯል፡፡ አምና 2008 . የእርሻ በሬው ቢሞትበት ከቆጠበው 9 ሺህ ብር አውጥቶ ፈረስ መግዛቱን አጫውቶኛል፡፡ ፈረሱ ለእርሻ ከሚሰጠው አገልግሎት በተጨማሪ አትክልትና ፍራፍሬ ለገበያ እያጓጓዘ ነው፡፡ በአሁኑ ሰዓት የጉና በጌምድር ወረዳ መናገሻ ከሆነችው ክምር ድንጋይ ከአባቱ ባገኘው የውርስ ቦታም ባለ60 ዚንጎ ቆርቆሮ ቤት ገንብቷል፡፡

ፕሮጀክቱ በሰጠው ስልጠናና የማዳቀያ ቁሳቁስ ድጋፍ አማካኝነት በአሁኑ ሰዓት አፕል እያዳቀለ ለመስሪያ ቤቶችና ለአርሶ አደሮች እየሸጠ በአማካይ በዓመት 4 ሺህ ብር ገቢ ያገኛል፡፡

አርሶ አደሩና ባለቤቱ / አለምናት 2005 . ጀምሮ "መጋቤ እንሰት" መንደር ተኮር ብድርና ቁጠባ ማኅበር አባል ሲሆኑ በድምሩ 5 ሺህ ብር ቆጥበዋል፡፡ በተጨማሪም በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 5 ሺህ ብር አስቀምጠዋል፡፡

አርሶ አደር ክንዳለም አማራጭ የሶላር ሃይል ተጠቃሚ በመሆኑ በየጊዜው ለነዳጅ የሚያወጣውን ገንዘብ አስቀርቶለታል፡፡ ልጆቹም ያለምንም የጤና ችግር ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ አስችሏቸዋል፡፡ በድህነቱ ምክንያት ተጠልቶ የነበረው አርሶ አደር ዛሬ የተለያዩ መስሪያ ቤቶችና አርሶ አደሮች ቀየውን የልምድ መቅሰሚያ ትምህርት ቤት አድርገውታል፤ እሱም ጎረቤቶቹን በማንቃት ተከታይ አፍርቷል። በአጠቃላይ አርሶ አደሩንና ማሳውን ለጎበኘ ሁሉ የአኗኗር ዘይቤው ምን ያህል እንደተለወጠ ለመረዳት አያዳግትም፡፡

 
ቋንቋ
ሶሻል ሚዲያ
FacebookTwitter
የጎብኝዎች ብዛት
Today3
Week118
All79216

Currently are 13 guests online


ምርጫ
ስለ ድረ-ገፅ ያለዎት አስተያየት ?