Joomla TemplatesBest Web HostingBest Joomla Hosting

ዋና ገፅ ዜና የቅርብ ዜናዎች አመልድ የመንግስትን የልማት ክፍተቶች በመሙላት ረገድ ከፍተኛ ሚና ያለው ድርጅት መሆኑን ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ገለጹ

Hi Slider ID 1

አመልድ የመንግስትን የልማት ክፍተቶች በመሙላት ረገድ ከፍተኛ ሚና ያለው ድርጅት መሆኑን ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ገለጹ

………………………….……//………………………………..

የአማራ መልሶ መቋቋምና ልማት ድርጅት (አመልድ) የክልሉን መንግስት የልማት ክፍተቶች ለመሙላት የጀመራቸውን የምግብ ዋስትና እና የልማት ስራዎች አጠናክሮ እንዲሰራ ከጥር 4-5/2009 ዓ.ም ኮምቦልቻ ከተማ በተካሄደው 2ኛው ልማታዊ የምግብ ዕርዳታ ፕሮግራም /Development Food Assistance Program (DFAP) II Launching Workshop/ የትውውቅ አውደ-ጥናት ላይ የተከበሩ አቶ ብናልፍ አንዱዓለም ተናገሩ፡፡

DEFAP II (1)DEFAP II (4)

ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ እንደገለጹት አመልድ በሚሰራቸው የተፈጥሮ ሃብት፣ ግብርና፣ ንጹህ መጠጥ ውሃና መስኖ አውታሮች የክልሉን አርሶ አደሮች ህይወት መለወጥ ችሏል ብለዋል፡፡

አቶ ብናልፍ በአውደ-ጥናቱ ለተገኙት የዞንና የወረዳ አስተዳድሮች፣ የሚመለከታቸው ሴክተር መስሪያ ቤቶች ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ከአመልድ እና ኤፍ ኤች ኢትዮጵያ ጋር በመቀናጀት ለ5 ዓመታት የሚቆየውን ፕሮግራም አርሶአደሩን በሚለውጥ መልኩ ውጤታማ ስራ ለመስራት ርብርብ ማድረግ እንደሚያሻ አሳስበዋል፡፡

የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር አምላኩ አስረስ በበኩላቸው 2ኛው ልማታዊ የምግብ ዕርዳታ ፕሮግራም በወርልድ ቪዥን አመቻችነት በአመልድ እና ኤፍ ኤች ኢትዮጵያ ፈጻሚነት ከአሜሪካ ዓለም- አቀፍ የልማት ተራድኦ ድርጅት በተገኘ ከ4 ቢሊዮን  ብር በላይ የገንዘብና የእህል ድጋፍ በክልሉ የዝናብ ዕጥረትና የምግብ ክፍተት ባለባቸው 13 ወረዳዎች ከ5 መቶ ሺህ በላይ ሰዎችን ተጠቃሚ ለማድረግ የሚተገበር ፕሮግራም መሆኑን አስረድዋል፡፡

                 DEFAP II (5)

ፕሮግራሙ በደቡብ ጎንደር 3፣ በሰሜን ወሎ 4 እንዲሁም በዋግኽምራ ዞን 6 ወረዳዎችን ያካተተ ሲሆን የነፍሰ-ጡሮችን፣ እናቶችንና ህፃናትን የጤና ሁኔታ ለማሻሻል፣ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋዎችን ለቋቋም የሚደግፉ ስራዎችን ለማስፋፋት እንዲሁም የአካባቢ ምርታማነትን የሚያሳድጉና ተጨማሪ የእርሻ መሬት የሚፈጥሩ የጠረጴዛ እርከን፣ የተፋሰስ ልማት፣ የአፈርና ውሃ ጥበቃ፣ የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦትና መስኖ ልማት ስራዎችን ትኩረት ሰጥቶ ይሰራል፡፡

የወርልድ ቪዥን ተወካይ ዶ/ር ጉቱ ቴሶ አመልድ ጠንካራ የልማት አጋር መሆኑን አውስተው 2ኛው ልማታዊ የምግብ ዕርዳታ ፕሮግራም በሚሰራባቸው አካባቢዎች ት/ቤቶችን፣ ጤና ኬላዎችን፣ አነስተኛና መካከለኛ ድልድዮችንና መስኖዎችን በማጠናከር የኅብረተሰቡን የኢኮኖሚና ማኅበራዊ ተጠቃሚነት እንደሚያሳድገውና ለቀጣይ የልማት ስራዎች መሰረት እንደሚጥል ጠቁመዋል፡፡

የዋግኽምራ ብሔረሰብ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ይልማ ወርቁ እንደተናገሩት ፕሮግራሙን ለማስፈጸም አመራሩና ሙያተኛው ግልጽ ሆኖ ተግባብቶና በዕቅድ አካትቶ መስራት ይጠበቅብናል ብለዋል፡፡

DEFAP II (2)DEFAP II (3)

በደሃና ወረዳ የግብርናና ገጠር ልማት ጽ/ቤት ኃላፊ የሆኑት አቶ ሰዒድ አባተ በአውደ-ጥናቱ የፕሮግራሙን ግቦች በውል መገንዘባቸውንና እ.ኤ.አ ከ2016 እስከ 2020 ዓመታት ለሚከናወኑ የልማት ስራዎች ከአመልድና ሌሎች ግብረ-ሰናይ ድርጅቶች ጋር ይበልጥ ተቀራርቦ ለመስራት እንደተዘጋጁ ተናግረዋል፡፡ በተለይ በ1ኛው ልማታዊ የምግብ ዕርዳታ ፕሮግራም ማገባደጃ የተገኘው ሳይንሳዊ የተፋሰስ ልማት ተጨማሪ የእርሻ መሬት በመፍጠሩ የሰብል ምርታማነትንና የዕርጥበት ዕቀባ ዘዴን ያሳደገ በመሆኑ በ28ቱ ቀበሌዎችና በ55ቱ የተፋሰስ ልማት ስራዎች ለማስፋት ዕቅድ መያዛቸውን ገልጸዋል፡፡

በመጨረሻም ፕሮግራሙ የአርሶአደሩን ህይወት በሚለውጥ አግባብ ለመፈፀም የወረዳና ዞን ሃላፊዎች የቃል-ኪዳን መግባቢያ ሰነድ በመፈራረም አውደ-ጥናቱ ተጠናቅቋል፡፡

Last Updated (Friday, 20 January 2017 13:45)

 
ቋንቋ
ሶሻል ሚዲያ
FacebookTwitter
የጎብኝዎች ብዛት
Today7
Week449
All71984

Currently are 18 guests online


ምርጫ
ስለ ድረ-ገፅ ያለዎት አስተያየት ?